Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

1 2,087

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፥ መንግስት ለህዝቡ ቃል በገባው መሰረት በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሀገርን በመዝረፍና የሀገሪቱን መፃኢ ተስፋ ለማጨለም የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲሁም የሰኔ 16 የቦምብ ፍንዳታን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን በማቀነባበር የተጠረጠሩትን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

መንግስት ይህንን እያደረገ ያለው በአንድ በኩል ባለፉት ዘመናት ህዝቡ በግልፅ ሲጠይቃቸው የነበሩ የፍትህ ጥያቄዎች በመሆናቸውእና በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ይህንን ለማድረግ ግዴታ ስላለበት እንደሆነም አስረድተዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የፍትህ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ መንግስትም የህዝብ ጥያቄ መመለስ ውዴታው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም እንደሆነ ገልፀዋል።

በአንድ ሀገር ውስጥ የመንግስት መኖርን የግዴታ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ፍትህን ማረጋገጥ እንደሆነም ገልፀዋል።

ፍትህ የሚረጋገጠውም ንጹሃን በኩራት ቀና ብለው የሚሄዱበትና ወንጀለኞች ደግሞ የትም የማይደበቁበት ስርዓት መፍጠር ስንችል ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች እንጂ ወንጀለኞች በኩራት የሚኖሩባት ሀገር መሆን የለባትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወንጀል የፈፀሙት እንዲቀጡበት፣ ሊፈፅሙ ያሰቡት እንዲጠነቀቁበት፣ እነርሱን ሊከተሉ የሚከጅሉት እንዲማሩበት ሲባል ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል፤ ተጀመረ እንጂ አልተፈፀመም፤ ዓላማውም በአራቱም አቅጣጫ ሀገሪቱን ከወንጀለኞች ነፃ ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ወንጀለኞች ጥቅም እስካገኙ ድረስ ወገኔ ለሚሉት አይራሩም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ወንጀለኛ ወገንም ብሄርም፣ ዘርም፣ ሞራልም የለውም ሲሉ አስታውቀዋል።

“ወንጀልና ካንሰር አንድ ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ካንሰርን በልምምጥ፣ በልመና እና በአማላጅ ማዳን አይቻልም፤ ካንሰርን በዝምታ መመልከትም ሞትን በእያንዳንዷ ቀን በዝምታ እንደ መጋበዝ ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

ካንሰር እንደወንጀለኛ ነው ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለራሱ ካልሆነ ስላለበት አካልም ሆነ ማንነቱን ስላአገኘበት የሰውነት ክፍል ፈፅሞ እንደማያስብ አስረድተዋል። ካንሰሩ ያንን የሰውነት ክፍል ለመኖሪያና ወደ ሌሎች ለመስፋፊያ ብቻ ነው የሚፈልገው ብለዋል።

ሁሉን ይጎዳል ብቻውን ይጠቀማል በማለት ነው ካንሰርና ወንጀል ያላቸው ቁርኝት በመግለጫቸው ያስረዱት።

ይህንንም ቁርኝት የወንጀልና የካንሰር መፈክሩ ሁሉን ለእኔ ሁሉን ወደ እኔ የሚል እንደሆነም ነው ያነሱት።

መግለጫው ካንሰር ስናክም ደህናዎቹ የሰውነት ክፍሎች ለጊዜው ይጎዳሉ በተለይ ካንሰሩ የጀመረበት አካል ክፍል የተጎዳ መስሎ ይታያል፥ እውነቱ ግን ከዚህ በተቀራኒ ነው በማለት ገልፀዋል።

የሰውነት ክፍሎቻችን በጥቂት የካንሰር ሴሎች ምክንያት እርስ በእርሳቸው አይጣሉም፣ አይባሉም፣ አይናከሱም፣ አይካሰሱም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እንዲያውም ካንሰሩን የጋራ ጠላት አድርገው በአንድነት ሊዋጉት ይነሳሉ ብሏል።

ምክንያቱም ካንሰሩ ከሰውነቱ ክፍል ስሙን እንጂ ሌላውን እንደማይወስዱ ያውቃሉ፤ እዚያ ቦታ መሽጎ ሁሉንም ሊያጠቃ እንደተዘጋጀ ያምናሉ ሲሉ አስረድተዋል።

እንዲሁም በእርስ በእርስ ፍትጊያ ጊዜ ማጥፋት ለካንሰሩ እደሜ መቀጠል መሆኑን ይረዳሉ፤ አብረው ተባብረው ካልተነሱም ዕጣ ፈንታቸው ሞት መሆኑን ይገነዘባሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ስለዚህ ሁሉም በተያዘው የሰውነት ክፍል ላይ ሳይሆን በካንሰሩ ሴል ላይ ለይተው እንደሚዘምቱ ነው ያመለከቱት።

ወንጀል ለፈፃሚው መጀመሪያ ጥቅም ያስገኘለት ቢመስለውም እየቆየ ግን ራሱን እየበላ ሄዶ መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል።

ወንጀል እንደካንሰር ነው ያልነው ለዚህ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወንጀለኛ የአንድን አካባቢ ህዝብ የሚፈልገው ሊጠቅመው፣ ሊሰራበት፣ ሊታገልለት ወይም ሊያለማለት አይደለም ብለዋል።

አራዊት እንኳን የማይፈፅሙትን ኢሰብዓዊ ድርጊት በሰው ዘር ላይ የሚፈፅም ሰው በምን አንጀቱ ለወገኑ ይራራል፣ በየትኛው ልቡ ለወገኑ ያስባል በየትኛውስ አእምሮ ለወገኑ ይቆረቆራል ሲሉ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥
ወንጀለኛ ማሰቢያው ጥቅም ብቻ ነው፤ ጥቅም ካገኘ ይዘርፋል፤ ያጠፋል፤ ይገላል፤ ያሰቃያል ያወድማል በማለት ነው ያብራሩት።

አሁን የተጀመረው ስራ ሀገር የገደሉ ወንጀለኞችን እነርሱ ለሌላው በነፈጉት ፍትህ ፊት የማቅረብ ስራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የተያዙ ሰዎችም በተገቢ ደረጃና አያያዝ የሚገባቸውን ፍትህ እንዲያገኙ ይደረጋልም ብሏል፡፡

እያንዳንዱ ማህበረሰብ የተሸሸጉትን ወንጀለኞች አጋልጦ ለህግ በማስረከብ ወንጀል የሚያሳፍር መሆኑን እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፥ የህዝቡ ትብብርም እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የወንጀለኞች መኖሪያ መሆን ያለባቸው ማረሚያ ቤቶች እንጂ ብሄሮች ብሄረሰቦች አይደሉም ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የቅጣቱ ዋና ዓላማ አጥፊዎችን መቅጣትና ድርጊቱን መኮነን ብቻ ሳይሆን ዳግም እንዳይከሰት መከላከልም ጭምር ነው ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

  1. Mulugeta Andargie says

    የሰረቀ፤ ያሳረቀ፤ ያሰራረቀ
    የደበቀ፤ ያጮለቀ፤ ያጯለቀ
    ሲጎርሱ፤ ያጎረሰ፤ የመረቀ
    እንዲያው ዝም ብሎም፤ ወግ የጠረቀ
    ተመልሶ፤ ያ ማጎሪያ ተጨናነቀ!!
    ከብት ተፈትቶ፤ ሲያበቃ
    ሰሞን ሳይሞላ፤ ታፍሶ እንደ ዕቃ
    ተግበስብሶ፤ እጨቃ
    ገርሞኛል! ከንእግዲህ! ሥራው ያውጣው! በቃ!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy