Artcles

ማን ከማን ጋር ነው—ጦርነት የሚገጥመው?

ማን ከማን ጋር ነው—ጦርነት የሚገጥመው?

By Admin

November 07, 2018

ማን ከማን ጋር ነው—ጦርነት የሚገጥመው?

                                                     እምአዕላፍ ህሩይ

 

“አንድን ፅሑፍ፤ ፋኖ፣ ቄሮ ወይም ዘርማ ወይም ሌላ የወጣት አደረጃጀት ለመፃፉ ማንም በርግጠኝነት መናገር በማይችልበት ሁኔታ፤ የተፃፈን ነገር ሁሉ አምኖ መቀበል ተገቢ አይደለም። የሚፃፈውንና በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቀውን ፅሑፍ በአንክሮ ማጤን ያስፈልጋል። ለምን ዓላማና ግብ እንደተፃፈም ማመዛዘን ይገባል። ያለ ሚዛናዊ ዕይታ በማይጨበጥ የወረቀት ላይ ጥሪ፤ አላስፈላጊ መንገድን መጓዝ አይገባም—የቁልቁለት ጉዞ ነውና።…”

 

ከመሰንበቻው የምሰማው ነገር የዚህ ሀገር አራዳዎች “አይነፋም” እንዲሉት ዓይነት ሆኖብኛል። አራዳዎቹ “ምቾት አይሰጥም፤ አያስደስትም” ማለታቸው ይመስለኛል—በእነርሱ ቋንቋ። ርግጥም የአንድ ሀገር ልጆች እርስ በርሳቸው በቃላት አንካሴ ሲወጋጉ፣ ሌሎችም የተፈጠረን ጊዜያዊ ችግር ወረቀት እየበተኑ ጭምር ለማጋጋል ሲሞክሩ መመልከት ምቾት የሚሰጥ አይደለም። እገሌ የተባለው ብሔር እገሌን ከአካባቢዬ ውጣ የሚል አስቂኝ ድርሰት መስማት ማንንም ሰላም ወዳድ ኃይል ሊያስደስት አይችልም።

በዚህ መሃል ደግሞ፤ አንዳንድ ወገኖች የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት ሲሉ፤ ማን እንደፃፈው የማይታወቅና ምንም ዓይነት ዕውቅና የሌለው አካል በየፌስ ቡክ ላይ የሚያዘዋውረውን የማስፈራሪያ ወረቀት ሲያቀርቡ ይስተዋላል። በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የተፈጠረውን ጊዜያዊ ጉዳይ ለማቀጣጠል ቤንዚን ከነዳጅ ማደያ ገዝቶ የማርከፍከፍ ያህል የሚቆጠር ነው።

ርግጥ ስለምንና ስለእነማን እያወራሁ እንደሆነ ለውድ አንባቢያን ግልፅ ይመስለኛል። አዎ! እያወራሁ ያለሁት ስለ ሰሞኑ የአማራና የትግራይ ክልሎች ሁኔታ ነው። የአማራና የትግራይ ህዝቦች ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የጋራ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ ያላቸው እንዲሁም ተዋልደውና ተጋብተው በአንድ ጎጆ ውስጥ የሚኑሩ ሁለት ህዝቦች፣ ግን ደግሞ አንድ ህዝብ ናቸው። ከሁለትነታቸው ይልቅ አንድነታቸው ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛል። በእኔ እምነት፤ ሁለቱን ህዝቦች እንደ ሁለት ከመመልከት እንደ አንድ ማየቱ ለሁሉም የሚቀል ይመስለኛል። በበኩሌ፤ የሁለቱ ክልል ህዝቦች በሁለትነት ከሚጠሩ፤ በአንድ የወል ስያሜ ተጠቃለው ቢታወቁ ማለፊያ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ከሚያለያዩዋቸው ይልቅ የሚያስተሳስራቸው የአንድነት ድር እጅግ የበረከተ ስለሆነ ነው። የጋራ ገፀ-በረከታቸው አብዝቶ የበዛ ነው።

ዳሩ ግን፤ እነዚህን በአንድነት ሊጠቃለሉ የሚችሉ ህዝቦችን፤ እርስ በርስ ለማባላት የሚቋምጡ ሃይሎች መኖራቸውን ማንም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ በቀላሉ ይገነዘበዋል። እንዲያውም በየማህበራዊ ሚዲያው ‘ለጦርነት መዘጋጀታቸውን’ የሚያውጁ አካላትን እየተመለከትን ነው። በፌስ ቡክና በሌሎች የትስስር መረቦች ላይ ሆን ተብለው እየተዘጋጁ የሚለቀቁ ፅሑፎች፤ ኢትዮጵያዊ አንድነት በሚነገርበት ሀገር ውስጥ ማፈሪያዎች ናቸው። ‘የእንቶኔና እንቶኔ ብሔረሰቦች አካባቢያችንን ለቅቃችሁ እንድትወጡ’ የሚል የአፓርታይድ ዓይነት አመለካከት፤ በዶክተር አብይ አህመድ መሪነት እየተቀነቀነ ያለውን የመደመር፣ የአንድነት፣ የኢትዮጵያዊነትና በጋራ ተሳስቦ የመኖር እሴቶቻችንን የሚመጥን አይደለም።

የውጭ ወራሪ ኃይሎችን በመመከት ለሚታወቀው የሀገራችን ህዝብ በኮንትሮባንድ የሚገቡ መሳሪያዎችን ሸምቶ የገዛ ወገኑን ‘ልወጋህ ነው’ ብሎ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም፤ ይህን ኩሩና የታፈረች ሀገር ህዝብ የሚመጥን አይደለም። ኢትዮጵያዊ የሚታወቅበት መለያው በባዕዳን ላይ አንድ ሆኖ በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ጠላትን ማርበድበድ እንጂ፤ ክላሽንኮቭ ጠብ-መንጃ ታጥቆ በገዛ ወገኑ ላይ ‘ውረድ እንውረድ’ ዓይነት ፉከራና ቀረርቶ ማሰማት አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ በራስ ወገን ላይ የሚደረግ ዛቻ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ኧረ ለመሆኑ የሚበጅ ነው ቢባል እንኳን ማን ከማን ጋር ነው ጦርነት የሚገጥመው?—በእውነቱ እንኳንስ በኢትዮጵያዊነት ወግና ባህል ተኮትኩተን ላደግነው ለእኛ ይቅርና ለሰሚውም ቢሆን ግራ የሚገባ አስተሳሰብ ነው። እናም ከዚህ ግራ ከሆነ እሳቤ በፍጥነት መላቀቅ ያስፈልጋል።

በየፌስ ቡኩ ላይ የሚንሸራሸሩ፣ ማን እንደ ፃፋቸው የማይታወቁና ምንም ዓይነት አስረጅ የሌላቸው እንዲሁም የአንድን ወገን ስም በመጥቀስ የሚፃፉና ምናልባትም በጥልቀት ለመረመራቸው ሰው ማን ሊፅፋቸው እንደሚችል በጉልህ የፊደል አጣጣላቸው ሊለዩ የሚችሉ ፅሑፎችም፤ ሀገራችን ውስጥ እየተገነባ ካለው ፌዴራላዊ ስርዓት አስተሳሰብ ጋር አብረው የሚሄዱ አይደሉም። የተጠቃሹን አካል ፍላጎትንና እምነትንም የሚያመላክቱ ናቸው ብሎ መውሰድ የሚቻል አይመስለኝም።

አንድን ፅሑፍ፤ ፋኖ፣ ቄሮ ወይም ዘርማ ወይም ሌላ የወጣት አደረጃጀት ለመፃፉ ማንም በርግጠኝነት መናገር በማይችልበት ሁኔታ፤ የተፃፈን ነገር ሁሉ አምኖ መቀበል ተገቢ አይደለም። የሚፃፈውና በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቀውን ፅሑፍ በአንክሮ ማጤን ያስፈልጋል። ለምን ዓላማና ግብ እንደተፃፈም ማመዛዘን ይገባል። ያለ ሚዛናዊ ዕይታ በማይጨበጥ የወረቀት ላይ ጥሪ፤ አላስፈላጊ መንገድን መጓዝ አይገባም—የቁልቁለት ጉዞ ነውና። በስንት መስዋዕትነት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም የተገኘን ነፃነት በወረቀት ላይ አሉባልታ ለመበተን መሞከር ከአላዋቂነት የዘለለ ትርጉም የሚያሰጥ አይደለም። ተግባሩንም ነፃነቱንና ባመጣው ኃይል ላይ በመለጠፍ እንደ ካሮት የቁልቁለት ጉዞ እንድንሄድ የሚሹ አካላት መናጆ መሆን የለብንም።

ርግጥ እነዚህ አካላት በፖለቲካው መስክ ያኮረፉ አሊያም የሀገራችን ጠላቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ አካላት ደግሞ የራሳቸው ግልፅና ስውር ዓላማ ያላቸው ናቸው። ይህንን እውነታ በሰከነ መንገድ መመልከት ያስፈልጋል። በአንድ በኩል፤ ‘እገሌ ከእገሌ ጋር ጦርነት ሊገጥም ነው’ የሚሉ ወሬን ያናፍሳሉ። ከፍ ሲልም፤ ህዝቦችን ከህዝቦች ለማጋጨት ወረቀት እየፃፉ ጭምር በየማህበራዊ ሚዲያው ይበትናሉ።

እነዚህ አካላት ወደ ብተና ሊያመራን የሚችልን ማንኛውንም ነገር ከመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም። ይህን አፍራሽ ተግባራቸውን ቆም ብሎ መመዘንና እነርሱ እንደ ቦይ ውሃ በፈለጉበት አቅጣጫ ወደሚወስዱን መንገድ ላለመጓዝ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለነገሩ ማንኛውንም የተፃፈን ነገር ሳናጣራ መቀበል መዘዙ የእርስ በርስ ፍጅት መፍጠር ብቻ የሚሆነው። ዜጎችን ወደ ግጭት በመውሰድ ሊጠቀሙ የሚችሉ ኃይሎች እየተፈጠረ ያለው ለውጥ፣ የሀገራችንና የህዝቦቿ ጠላቶች ብቻ ናቸው። ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና የሚያስቡ አካላት ህዝቦችን የሚያቃቅሩና ከፍ ሲልም ወደለየለት ቀውስ ወደሚከቱ ተግባሮች ላይ አይሰማሩም። እናም ወገኔ ሆይ! ዓይንህን ክፈት፣ ንቃ፣ አስተውል።

በመጠላላትና በመጠላለፍ ብሎም ለጦርነት በማሰፍሰፍ የሚጠቀም የትኛውም ወገን የለም። ምናልባት እንደ ጥቅም የሚወሰድ ከሆነ፤ ጥቅሙ ሊሆን የሚችለው የሌሎች መጠቀሚያ ሆኖ ሀገርን መበተን ብቻ ነው። ኢትዮጵያ እንድትበተን የማንኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ ፍላጎት ሊሆን አይችልም። ይህን መሰሉ ፍላጎት በተፈጠረው ሀገራዊ ለውጥና በህዝቦች ላይ የቅርብና የቆየ ቁርሾ ያላቸው ኃይሎች ብቻ ነው። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ ማን ከማን ጋር ነው—ጦርነት የሚገጥመው? ብለን ብንጠይቅ፤ ምላሹ ሊሆን የሚችለው “እኔ ከእኔ ጋር” የሚል መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ እኔ ከእኔ ጋር ጦርነት ላካሂድ አልችልም። እብድ ካልሆንኩ በስተቀር ፤የራሴን እጅ በራሴ ልቆርጠው አልችልም። ኧረ እብድም ቢሆን ሊያደርገው የሚችል አይመስለኝም። ትናንት በክፉ ቀን አብሬው የነበርኩትን ወገኔን ‘ካጠገቤ ዞር በል’ ልለው አልችልም። ምክንያቱም ‘ዞር በልልኝ’ የምለው ራሴን ነውና። የራሴን አካል፣ ሰውነቴን፣ እኔነቴን ከራሴ ነጥዬው እንዲያ ልለው ከቶ እንደምን ይቻለኛል?—በፍፁም አይቻለኝም። ሰናይ ጊዜ።