የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴት ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነ ገበየው አዲስ ለተሸሙትና ለነባር አምባሳደሮች በተዘጋጀው ስልጠና መድረክ ላይ ሀገርን መወከል ከባድ ሃላፊነት መሆኑን ተናገሩ፡፡
ይህ ስልጠና በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን በዋናነት ግን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማስከበር ዙሪያ የሚጠበቅባቸው ሀላፊነትና ለዜጎች በሚሰጠው ትኩረት ላይ የሚያተኩር ይሆናል፡፡
ዶ/ር ወርቅነ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት ሁሉም አምባሳደሮች ለሀገራቸው ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው በማሳሰብ በሚሄዱባቸው ሀገራት የሀገራቸውን ባህልና ወግ በሚገባ ማስተዋወቅና የሚፈጥሩት ዲፕሎማሲ ከእጅ መጨባበጥ ያለፈ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ ምሁራንና የሙያው ጠበብቶች ስልጠናውን የሚሰጡ ይሆናል ፡፡
ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 1ቀን2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን በመጨረሻ ቀን የሁሉም አምባሳደሮች ባሎችና ሚስቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡