Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

<<ቃልን ማጠፍ በኦሮሞ ባህል የተለመደ አይደለም>> አቶ ገላሳ ዲልቦ የሽግግር አካል ኦነግ ሊቀመንበር

0 1,443

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በትግል ውስጥ ወደ 45 ዓመታት ያህል ቆይተዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታትም በውጭ አገር የቆዩ ሲሆን፣ ወደ አገር ቤት የገቡት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ በታህሳስ ወር ማጠናቀቂያ ላይ ነው – አቶ ገላሳ ዲልቦ ፡፡

ለራሳቸው የሚበቃቸውን ያህል መማራቸውን ይገልጻሉ፤ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ የሚመነዘር እውቀት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በትግል የቆዩበት ድርጅት በዋናነት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ ሲሆን፣ እሳቸው የሚንቀሳቀሱበት ኦነግ ‹‹የገላሳ ኦነግ›› ተብሎ ይጠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ግንባሩ አሁን የያዘው ስያሜ የሽግግር አካል ኦነግ የሚባል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአገራዊ ለውጡ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከአቶ ገላሳ ዲልቦ ጋር ያደረገውን ቆይታ  እንደሚከተለው  አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የድርጅትዎ ስያሜን በተመለከተ አጭር ማብራሪያ ቢሰጡን?

አቶ ገላሳ፡- የድርጅቱ ስም ኦነግ ሲሆን የራሱ ትርጓሜም አለው፡፡ ድርጅቱ ተለይቶ ይታወቅ የነበረው የገላሳ ኦነግ እንዲሁም የዳውድ ኦነግ በሚል ነበር፡፡ የሽግግር አካል ኦነግ የተባለውም ስያሜ ከሌሎች ጋር  ሰላም አውርደን ድርጅታችንን ወደነበርበት እንመልሳለን ብለን ስንታገል ነበር፡፡ የሽግግር አካል ኦነግ የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎና ድርጅትዎ ወደ አገር ቤት የመጣችሁት ምን ዓይነት አቋም ይዛችሁ ነው?

አቶ ገላሳ፡- አገር ቤት ያለውን ሁኔታ ስንከታተል ነበር፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ንግግር ካደረጉ በኋላ ምን እንደታሰበ ተገንዝበናል፡፡ ሲወሰዱ የቆዩ ዕርምጃዎችንም ስንከታተል ቆይተናል፡፡ በዚህም የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ በአሸባሪነት ተፈርጀው በነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የተወሰዱትን ዕርምጃዎች ተረድተናል፡፡

‹‹በአገሪቱ የሰላም ነፋስ መንፈስ አለበት፤ ይህ ለውጥም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል አለበት›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር በጥልቀት የተጀመረውን ለውጥ እንድንቃኝና እንድንደግፍ አድርጎናል፡፡ ሀገሪቱን ከአምባገነኖች መዳፍ አውጥተን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር መጓዝ አለብን፤ የሰብዓዊ መብት ረገጣ መቆም አለበት፡፡ በየአገሩ ተሰደውና ተገፍተው የወጡት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና አባሎቻቸው  ተፎካካሪ ስለሆኑ ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ አለባቸው የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም አጽንኦት ሰጥተን ተመልክተነዋል፡፡

ከዚህ በመነሳትም ባወጣነው መግለጫ የሚታየው ሁኔታ ጥሩ ጅምር መሆኑን በመጥቀስ እንደምንደግፈውም አረጋግጠናል፡፡ ወደ አገራችን ተመልሰን በተጀመረው ለውጥ ውስጥ መሳተፍ በምንችልበት ሁኔታ ላይ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት ስንሠራ ቆይተናል፡፡

በዚሁ መሰረትም እ.ኤ.አ ህዳር 30 ቀን 2018 በጀርመን በርሊን ከተማ ከመንግሥት ወገን ከእነ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ እንዲሁም በኢፌዴሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተመራው ልዑክ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያየተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡-በውይይታችሁ ካነሳችኋ ቸው ነጥቦች መካከል የተወሰኑትን ቢያብራሩልን?

አቶ ገላሳ፡- ከተወያየንባቸው ነጥቦች መካከል አንዱ በኦነግና በመንግሥት መካከል ለ20 ዓመታት በጦርነት ስንፈላለግ የነበረበት ሁኔታ እንዲያበቃ  ማድረግ የሚለው ነው፡፡ እኛም የራሳችን ዓላማ አለን፤ ይህ ዓላማችን አመለካከታችንን ያለአንዳች ጫና በሰላማዊ መንገድ በአገር ውስጥ ማራመድ የምንችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ በሁለታችንም በኩል ኃይል መጠቀም የሌለብን መሆኑ ላይም ተወያይተናል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የት እንደገቡ ያልታወቁ የኦነግ እስረኞች ጉዳይ ነው፡፡ ስለ እነዚህ ዜጎች መንግሥት አያውቅም ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ ሰዎች የት እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ማረጋገጥ አልቻሉም፤ ይህ ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ በጦርነቶች የተጎዱ ወታደሮች በርካታ ናቸው፡፡ በተለያዩ ቦታዎችም ተበታትነው ዕርዳታ የሚሹ አሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እነዚህን ዜጎች እንዲያፈላልግ ጥያቄ አቅርበን መክረናል፡፡

ብዙ ወታደሮቻችን ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል፤ ራሳቸውንም መርዳት አቅቷቸው የድሃ ቤተሰቦቻቸው ጥገኛ ሆነው በአስከፊ ህይወት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህም ሊደረግ የሚገባ ካለ ከመንግሥት ጋር መፍትሔ ማፈላለግ የሚሉና መሰል ነጥቦችን አንስተን ከስምምነት ለማድረስ ነው ወደ አገራችን የመጣነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎና የሚመሩት ድርጅት በኦሮሞም ሆነ በሌላው ዘንድ ትልቅ ስም አላችሁ፡፡ ከእርስዎና እርስዎ ከሚመሩት ኦነግ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይጠበቅ? አቶ ገላሳ ለዚህች አገር ምንድን ነው ይዘው የመጡት?

አቶ ገላሳ፡- ከእኛ ይልቅ ትልቁ ህዝብ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ነው ትልቅ እንጂ እኛ ያን ያህል አጃኢብ የሚያስብል ሥራ ሠራን ብለን አናስብም፡፡ ለህዝቡ ትልቅ ክብር አለኝ፡፡ ህዝቡ ምን ይዘህ መጣህ የሚለኝ ከሆነ የህዝቤ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ አንዱ ዋና ትኩረቴ ሰላም መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ በእርግጥ ችግሮችም እያሉ የሚታይ ለውጥ አለ፡፡ ችግሩን ደግሞ ታግለን ልንፈታው እንችላለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ፓርቲዎች ቃላቸውን ሲለውጡና ሲያጥፉ ይስ ተዋላሉ፡፡ እርስዎ አዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ገላሳ፡- ቃልን ማጠፍ በኦሮሞ ባህል የተለመደ አይደለም፡፡ ቃል የተግባቡ አካላት  የሚስማሙበትን ጉዳይ አስቀድመው በሚገባ ሊያውቁትና ሊረዱት ይገባል፡፡ አንድ ነገር ላይ ተግባብተናል ከተባለ በኋላ ወደ ተግባር ሲገባ የሚያጋጥም ክፍተት ካለ ለመሙላት መመካከር ያስፈልጋል፡፡

እኔ ይህን ነገር በጥቅሉ ማየት የምፈልገው ለኔ ከምንም በላይ ትልቁ ነገር አንድ የለውጥ ሂደት መጀመሩ ነው፡፡ እኛም ይህንን ጉዳይ አምነን ነው የመጣነው፡፡ ከመጀመሪያውም እንዴት ነው እየሄደ ያለው የሚለውን ስንከታተል ቆይተናል፡፡ ይህ ለውጥ ከተሳካ ህዝባችን (ኦሮሞም ይሁን ሌላው ህዝብ) ንዴቱን ያበርዳል፤ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው ጥያቄውም መልስ የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡

እናምናለን ስንል ደግሞ ባለንበት ሆነን የሚመጣውን ሁሉ እንጠብቃለን ማለት አይደለም፡፡እንድንበረታ የተገኘውን ዕድል በመጠቀም ግዴታችንን መወጣት ይገባናል፡፡

አንድ ስርዓት ተወልዶ ለውጥ በታየ ቁጥር የፖለቲካ ምህዳሩም እያሰፋ ይሄዳል፡፡ በዚያ ውስጥ ደግሞ እኛም ድርሻ ይኖረናል፡፡ በዚህም ድርሻችን  የአቅማችንን ያህል ተጠናክረን በመሥራት የተገኘው ዕድል እንዲሰፋ እና ለውጡ ወደኋላ እንዳይመለስ ድጋፍ በማድረጉ እንጠብቀዋለን፡፡

መንግሥትን ይህንና ያንን ካላደረግክልን በስተቀር ይህንን አናደርግም የሚል አካሄድ አንከተለም፡፡ ዕድሉ ተፈጥሯል፤ እኛም ዕድሉን አግኝቶ የተለወጠው አካል እንደተደሰተው ሰው ሁሉ እንደሰታለን፡፡

ይህችን አገር ወደ ዴሞክራሲ እናሸጋግራለን የሚል እቅድ ተይዟል፡፡ ይህን ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ለምን ቢባል የዚህቺን አገር አጠቃላይ ሁኔታ  ስናይ እንደ ፋሽን የመጣውን አዲስ ርዕዮተ ዓለም ሁሉ በመውሰድ እንታወቃለን፡፡ ሶሻሊስቱ ሲመጣ ሶሻሊስት እንሆናለን፤ ሌላውም ሲመጣ እንዲሁ እሱን እንወስዳለን፡፡ ዴሞክራሲ ነው ሲባልም ደግሞ እንዲሁ ለማድረግ እንሮጣለን፡፡

ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትን በእጅጉ ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲን ለመገንባት በራሱ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል፡፡

ለምን መጣችሁ ከተባልን በመጀመሪያ ደረጃ የመጣነው ለሰላም ነው፡፡ ይህን ስንል ደግሞ ለሰላም እንታገላለን ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር አቀፍ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው አሃዳዊ ስርዓት እንጂ ፌዴራሊዝም አይደለም ይላሉና ለዚህች አገር የሚያስፈልገው የቱ ነው ይላሉ?

አቶ ገላሳ፡- አንዳንድ ሰዎች ብዙ ተደክሞበት የተገኘውን ለውጥ ወደኋላ ለመመለስ ያስባሉ፡፡ እኔ ከፌዴራሊዝም ችግር የለብኝም፡፡ የዚህች አገር ችግር ፌዴራሊዝም አይደለም፡፡ ደግሞም ለዚህች አገር ፌዴራሊዝም ሲባል በአፍ የሚነገር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የምናስተውል ከሆነ እኮ ፌዴራሊዝም የሚባለው በሰው አዕምሮ ውስጥ ሳይሆን ያለው አንደበት ላይ ብቻ ነው፡፡

የኦሮሞ ህዝብ አለ፤ህዝቡም የኦሮምኛ ቋንቋን ይናገራል፡፡ የፌዴራል አወቃቀር ወይም አሠራር ደግሞ በእኛ አገር ብቻ አይደለም ያለው፤በተለያዩ አገራት አለ፡፡ እንዲህ አይነቱ አወቃቀር በአውሮፓም፣ ካናዳ፣ ሲውዘርላንድ፣ ቤልጄየም፣ ሆላንድ ወዘተ አለ፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝም በብዙ አገሮች አለ ማለት ነው፡፡

የእኛ የተለየ አይደለም፡፡ ስለዚህም ፌዴራሊዝም ችግር የሚያደርስብን ስርዓት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ አገር ናት፡፡ የትኛውም ብሄር ደግሞ ትንሽ ትልቅ ተብሎ ሊፈርጅ አይችልም፡፡ ሁሉም ብሄር እኩል ነው፡፡ የበታችና የበላይ የሚባል ነገር በብሄር መካከል የለም፡፡ ሁሉም በየቋንቋው የራሱን ማንነት መግለጽ ይችላል፡፡

ሁሉም ብሄር አለባበሱን ብቻ የሚያሳይ ሳይሆን በፍርድ ቤት እኩል የሚዳኝበት፣ በራሱ ቋንቋ የሚማርበት ሁኔታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ስለዚህም ይህ ስርዓት የሰጠው ዕድል ከሆነ በዕድሉ መጠቀም መቻል ማለት ህዝቡን ለማሳደግና ወደፊት ለማራመድም እንደሚያግዝ ይሰማኛል፡፡

ሀገሪቱ ፌዴራሊዝም ሳይሆን አሃዳዊ ስርዓት ነው የሚያስፈልጋት የሚሉ አካላት ከምን ተነስተው ይህን ማለት እንደፈለጉ አላውቅም፡፡ ይህንን ስርዓት ያመጣው ራሱ የህዝብ ጥያቄ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ስለዚህም አገሪቱ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች አገር መሆኗን ልንቀበል ይገባል፡፡ እነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳይባሉ እኩል ናቸው፡፡

ትንሽ ብለው የሚጠሯቸው ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉ ትልቅ ናቸው ተብለው ከተፈረጁት ጋር እኩል ናቸው፡፡ ይህንን ጠንቅቆ ማወቅ የሰላም መሰረት ነው፡፡ እኛ እንዳልንህ ትተዳደራለህ ማለት ሰላም ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከዚህ በፊትም ተሞክሮ ስኬታማ መሆን ያልቻለ አካሄድ ነው፡፡ ስለዚህም ከወዲያ በኩል ያለው ሐሳብ የራሱ ሐሳብ ነው፡፡ እኔ ግን በፌዴራሊዝም ላይ ጥያቄ የለኝም፡፡

ፌዴራሊዝም ለዚህች አገር ጠቃሚ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ፣የለም አይጠቅማትም የሚሉ እንዳሉም ግልጽ ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን የማይጠቅም መስሎ ከተሰማው እስከአሁንም አልፈልግም ባለ ነበር፤ግን አላለም፡፡ ባይፈልግ ኖሮ መንግሥትን ያፈርስ ነበር፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝም በችግር ውስጥ የቆየውን ስርዓት የገረሰሰ፣ ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ብሄሮች ፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ችግር አሸንፎ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ማስኬድ ያስቻለ ስርዓት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዜግነት ወይም ብሄር መሰረት ያደረገ ፓርቲ አመሰራረትን እንዴት ይመለከቷቸዋል?

አቶ ገላሳ፡- ፓርቲዎች እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ሊመሰረቱ ይችላሉ፡፡ አንድ ፓርቲ የብሄርን አጀንዳ አራምዳለሁ፣ ለትልቅነቱ እሠራለሁ አሊያም የምከላከልለት ነገር ይኖረኛል በሚል  ሊቋቋም ይችላል፡፡ አገር አቀፉም ቢሆን መሰል ጉዳዮችን ይዞ ይገነባል፡፡

አገር አቀፉም ሆነ ብሄር ተኮሩ ፓርቲ የየራሳቸው ችግር ይኖርባቸዋል፡፡ ሁለቱም ግን ሳይለያዩ አንድነታችንን የሚያጠናክሩበትን ሁኔታ መሥራት ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ሰዎችን ሳይለያዩ በአንድነት መያዝ በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም የሚያስፈጽሙት እቅድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን ሁለቱም በያዙት ፕሮግራም ይለካሉ፡፡

አዲስ ዘመን፦ በለውጡ ላይ የሚታይ ተሰፋና ስጋት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ገላሳ፡- ለውጡ በመልካም መንገድ ላይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምን ሐሳብ አለህ የምባል ከሆነ ለውጥ ሁሌም በፈተና ውስጥ አልፎ ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ለውጥ ሁሌም ቢሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል መዘንጋት የለበትም፡፡ በለውጥ ውስጥም ተግዳሮት እንዳለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለውጡ ስኬታማ ይሆን ዘንድ መንግሥትም አንዳንድ ዕርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል፡፡

በለውጡ ባልተደሰቱ ሰዎች ሳቢያ ለውጡ ከመጣ አንስቶ አገሪቱ ሰላሟን አጥታለች፤ መረጋጋትም አይታይባትም፡፡ ይህን ተከትሎም እነዚህ ሰዎች አሁን ያለው መንግሥት ደካማ ነው፡፡ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ የሚያስፈ ልገው ጠንካራ መንግሥት ነው እያሉ ናቸው፡፡

ጠንካራ መንግሥት ሲሉ ምን ማለታቸው ነው ስንል ከቀድሞ ስርዓት የመጡ እንደመሆናቸው ጠንካራ መንግሥት ብለው የሚያምኑት በጉልበት ሲገዛና ሲያስተዳድር የነበረውን ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በስጋት ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ ይሁንና ለውጡን አጠናክሮ በመቀጠል ስጋትን ማስወገድ ይቻላል፡፡ ለውጡን አቅልሎ ማየት አይገባም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለውጡን አመጡ ከሚባሉት መካከል ቄሮዎች፣ ፋኖዎችና ዘርማዎች ይጠቀሳሉና በቀጣይ እነዚህ ወጣቶችም ሆኑ ህዝቡ ምን እንዲያደርግ ይጠብቃሉ?

አቶ ገላሳ፡- ወጣቱን በእርግጥ እንዲህ አድርግ ማለት ባልችልም ለውጡ የመጣበት መንገድ ይታወቃልና ይህ መዘናጋት እንደሌለበት እመከረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለምሳሌ አምቦ፣ ጭናክሰን፣ ደምቢዶሎ፣ ሞያሌ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የተደረገውን ሁሉ ማስታወስ ይገባል፡፡ ከእነዚህ ተግዳሮቶች በኋላ ነው ይህን ለውጥ ማየት የቻልነው፡፡ እንዲህ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘውን ለውጥ እንደዋዛ ማየት ሳይሆን ለሰላም ተጠናክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በጥቃቅን ነገሮች እየተደለሉ ወደኋላ መሄድ ሁሉንም የሚያጠፋ ጎርፍ ነው፡፡  ይህ እንዳይሆን በአስተውሎት መራመድ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ለውጡን ከአደናቃፊዎች መጠበቅና የበለጠ ስኬታማ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ እንረዳለን፤ ለስኬታማነቱም ወጣቶችን ጠንክራችሁ መሥራት አለባችሁ እላለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በ2012 የሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይካሄዳል የሚል እምነት አለዎት?

አቶ ገላሳ፡- ወደ አገር ቤት የመጣነው በቅርብ ስለሆነ ምርጫ 2012ን በተመለከተ መረጃ ስለሌለን አሁን እንዲህ ነው ብዬ መናገር አልችልም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት የራሱን አጀንዳ ይዟል፡፡ ምርጫው መካሄድ ይችላል አይችልም ብሎ ለመናገር በመጀመሪያ ይህንን መረዳትን ይጠይቃል፡፡

ስለምርጫው ለመናገርም በመጀመሪያ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችንና ሌሎችን ማወያየት ይጠበቅብናል፡፡ እናም ይህ የምርጫ ጉዳይ የፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይ ለመናገር በቅድሚያ የራሳችንን ጉዳይ ገምግመን ቢሆን ይመረጣል፡፡ ስለዚህም አሁን ምርጫው ይካሄዳል አይካሄድም ብሎ መናገር ያስቸግራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

አቶ ገላሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011

አስቴር ኤልያስ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy