Artcles

“ሹክሹክታ”—ልሳነ አሉባልታ

By Admin

January 17, 2019

“ሹክሹክታ”—ልሳነ አሉባልታ

                                                 እምአዕላፍ ህሩይ

ሰሞኑን አንድ አስገራሚ የወሬ ድሪቶ ሰምቻለሁ—የአሉባልታ ቋት ከሆነው “ሹክሹክታ” ከተሰኘ የወሬ ማህደር። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሆኖ የባጥ የቆጡን የሚያነበንበው አንሸኳሻኪው፤ አንድ ጉዳይ ካገኘ፤ ነገሩን እያጣመመ እርሱ ለሚፈልገው ዓላማ በማዋል በግለሰቦች ላይ መለጠፍ ስራዬ ብሎ የተያያዘና ቅንጣት ያህል ኃላፊነት እንኳ የማይሰማው የግለሰቦች ስብስብ ሚዲያ ነው።

በተለይም ከአንዳንድ አካላት የተሰጠውን ለውጥን የማደናቀፍ ዓላማ ለማሳካት ሲል በስራ ባተሌ ሆነው፣ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን አደራ ለማሳካት ደፋ ቀና የሚሉ እንደ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ዓይነት ግለሰቦችን ከአንድ ድርጊት ጋር እያቆራኘ ሆን ብሎ ጥላሸት እየቀባ መዋል መደበኛ ስራው አድርጎታል። ርግጥ ሚዲያው ‘የግለሰቦችን ስም እየደጋገመ ለምን ያነሳል?’ ብሎ የጠየቀ ማንኛውም ሰው፤ አንሸኳሿኪው ከምናውቃቸውና ለውጡን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው በመስራት ላይ ከሚኙት ከእነ “አያ እንቶኔ” ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው እንዲሁም በእነርሱም እየታዘዘ ይህን መሰል ተግባር እንደሚፈፅም በቀላሉ መገንዘቡ አይቀርም። ምክንያቱም “ምግባርህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” እንዲሉ ታታሪዎቹ ጃፓኖች፤ አንሸኳሿኪው ሚዲያ የሚያከናውነው ተግባር ማንም ሳይጠይቀው ራሱ እጁን አውጥቶ የሚናገር ስለሆነ ነው።

ታዲያ ለዚህ አባባሌ አንባቢዎቼን ሩቅ በመሄድ ላደክማችሁ አልሻምም—ይኸው ሚዲያ በአንድ ወቅት ዶክተር ወርቅነህን በሚያስቅ ሁኔታ “ኦሮሞ አይደሉም” በማለት “አራምባና ቆቦ” ምክንያቶችን እያቀረበ ሌላ ማንነት ሊሰጣቸው ሲከጅል ተመልክተናልና። ሰሞኑን ደግሞ፤ በምርጫ 97 የተፈፀመን ጉዳይ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከእርሳቸው ጋር በማቆራኘት ላም ባልዋለበት ኩበት ለመልቀም ሲሞክር ታዝቤዋለሁ። ነገሩ “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” የሚባለውን የናዚ ተረክ ተከትሎ የሚከናወን ተራ ፕሮፖጋንዳ ነው ማለትም ይቻላል። ዳሩ ግን፤ ውሸት መቼም ቢሆን የእውነት መንደር ውስጥ ድርሽ ልትል እንደማትችል አንሸኳሿኪው ምንደኛ ሚዲያ የገባው አይመስለኝም።  

የአንሸኳሿኪው ሚዲያ አስገራሚ ነገር፤ በአደባባይ በዜና የተነገረን ሃቅ ከዶክተር ወርቅነህ ጋር የግድ አጣብቆ በመስፋት “ሹክሹክታ ነው” ሊለን ሁሉ መዳዳቱ ነው። “አይ አለማፈር” አሉ ሼህ ከድር። በመገናኛ ብዙሃን የተነገረ አንድ ጉዳይ እንደምን መንሾካሾኪያ ሊሆን እንደሚችል የሚያውቀው አንሸኳሿኪው ቡድን ብቻ ቢሆንም ቅሉ፤ በበኩሌ ግን፤ በየጊዜው በግለሰቦች ላይ የውሸት አንካሴን እየወረወረ ለሚኖር አካል ለሃቅ ሲባል ምላሽ መስጠት ይገባል ብዬ አምናለሁ—ምንም እንኳን ሐሰትን መዘላበድ የሚዲያው ‘የዕለት እንጀራ’ ቢሆንም። ነገሩ እንዲህ ነው።…

አንሸኳሻኪው እንዳለውና እኔም በመገናኛ ብዙሃን እንደሰማሁት፤ የተወሰኑ ግለሰቦች ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ጥቆማ ያቀርባሉ። ጥቆማው በምርጫ 97 ወቅት በመንግስት ስለተፈፀሙ ተግባሮች የሚያወሳ ነው። የተወካዩች ምክር ቤትም ጥቆማውን አክብሮ በመቀበል ወደ ህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ይመራዋል። ቋሚ ኮሚቴውም ጉዳዩን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ፤ “1ኛ/ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ጥቆማው ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዱቀርብ፤ 2ኛ/ የወንጀል ጉዳዩችን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እያከናወነ ባለው ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሂደት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፤ በዚሁ አግባብ እንዲታይ ቢደረግ፤ 3ኛ/ በወቅቱ በአዋጅ ቁጥር 478/1998 የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን፤ በጊዜዊነት ተቋቁሞ ስራውን በማገባደድ ህልውናው ያከተመ በመሆኑ፤ አሁን ላለው ምክር ቤት ሪፖርት የሚያቀርብበር የህግ መሰረት የለውም። በእነዚህ ሶስት ምክንያቶች ለጥቆማው ምላሽ የተሰጠ መሆኑን እንገልፃለን” የሚል መልስ ሰጥቷቸዋል። በእኔ እምነት፤ ምክር ቤቱ ትክክል ነው። ምክንያቱም ግለሰቦቹ ተፈፅሟል የሚሉትን የህግ ጥሰት ካለ የተጣራ መረጃና ማስረጃ በመያዝ ማቅረብ የሚገባቸው ለሚመለከታቸው አካል በመሆኑ እንዲሁም ላልወከላቸው ምክር ቤት ሪፖርት የማቅረብ ህጋዊ ስልጣን የሌላቸው በመሆኑ ነው። ያም ሆኖ፤ ግለሰቦቹ ‘ፓላማው የእኛን ሪፖርት ካልተቀበለ ሞተን እንገኛለን’ ባይ ሆነዋል። እንዲህ ዓይነቱ ፍትህን በኢ-ፍትሃዊነት ለማግኘት መጣር ከወያኔው አገዛዝ ጋር አብሮ ያከተመ መሆኑ የገባቸው አይመስለኝም። ዳሩ ግን፤ ምስጋና ለለውጡ ቀንዲሎች ይግባቸውና በሀገራችን የዴሞክራሲ ድባብ እየሰፈነ በመሆኑ፤ ጥያቄያቸውን በህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ መብታቸው መሆኑን በግሌ ላስታውሳቸው እወዳለሁ።

የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰትንና ወንጀልን በእጅጉ እኮንናለሁ። ሚዲያዎች የማይገናኙ ጉዳዩችን እየመዘዙ ሰዎችን ለማጥቃት ለማጥቃት የሚያከናውኑትን ተግባር በዚያውኑ ልክ እንደ ዜጋ እቃወማለሁ። ዛሬ የለውጡ ሐዋሪያ የሆኑት ቲም ለማና ተከታዩቻቸው፤ ስለ ፍቅር፣ ስለ ይቅር ባይነት፣ ስለ አንድነትና ስለ መቻቻል እየሰበኩ ባሉባት ሀገራችን ውስጥ፤ ምንደኛ ሚዲያዎች የራሳቸው ዓላማ ባላቸው ኃይሎች እየታገዙና የጥላቻ ፈረስ ላይ ቁጭ ብለው በሚጋልቡ ግለሰቦች እየተመሩ ለውጡን ለመግፋት የሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት ያመኛል። “ሰይጣን ላመሉ ከመፅሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” እንዲሉ፤ አንሸኳሻኪው ሚዲያ፤ የዶክተር አብይን ወርቃማ ንግግሮች ለሚፈልገው የስም ማጥፋት ዘመቻ ቆርጦ በመቀጠል እየተጠቀመ የለውጡን ሃዲድ በአሉባልታዊ የሹክሹክታ መጋዝ ሊገዘግዘው ሲሞክር መመልከትም ለውጡን እንደሚደግፍ ዜጋ በዝምታ ማለፍ ተገቢ አይደለም።

በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የተሰባሰበው አንሸኳሿኪ ቡድን፤ ባለው አቅም ሁሉ ለውጡን ለማደናቀፍ የተሰለፈ ኃይል ነው ብዬ አምናለሁ። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ባለፉት ጊዜያት ለተፈፀሙት ተግባሮች ሁሉ ህዝቡን በይፋ ጠይቋል። ኢህአዴግ ደግሞ ግዑዝ አካል አይደለም—ህጋዊ ሰውነት ያለው የሰዎች ስብስብ እንጂ። እናም ይቅርታው በድርጅቱ ውሰጥ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ የሚያካትት ነው። ይቅርታው ‘ከ—-እስከ’ ድረስ ነው። አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚባል ነገር የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ታዲያ እዚህ ላይ ግለሰቦች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትም ይሁን ወንጀል ከፈፀሙ፤ በተረጋገጠ መረጃና ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ መጠየቅ አይቻልም እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። በምርጫ 97ትም ይሁን በምርጫ 2002 ወቅት በተፈጠሩት ክስተቶች ማን ምን አደረገ?፣ ለተፈፀሙ ተገቢ ያልሆኑ ተግባሮች በትክክል ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው አካል ማነው?፣ አፈፃፀሙስ እንዴት ነበር?፣ በምን ዓይነት የዕዝ ሰንሰለት ተግባሮች ይፈፀሙ ነበር?…ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት፤ ነገሮችን በጥሞና መመልከት ሲገባ፤ በጥላቻ ፖለቲካ ተመርኩዞና ያለ አንዳች አስረጅ ሰውን በሚዲያ ላይ ያለ ግብሩ ስም መስጠት በራሱ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን መገንዘብ አግባብ ይመስለኛል። 

  

ያም ሆኖ፤ ልሳነ አሉባልታው ሹክሹክታ፤ የፈጠራ ፊልምንና ድምፅን በመጠቀም “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ዓይነት ትረካዎችን በማቅረብ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ላይ እያከናወነ ያለው የአሉባልታ ተግባር ተራ ሴራ ከመሆን የሚዘል አይደለም። በበኩሌ፤ የዶክተር ወርቅነህ ባህሪ እነ ሹክሹክታ እንደሚያወሩት የአሉባልታ ትረካ አይደለም። ለዚህ ደግሞ እማኜ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው— በአንድ ወቅት የሰውዬውን ሆደ ቡቡነት ሲመሰክሩ ሁላችንም አድምጫለሁና። ለሰው የሚያዝኑና ቅን የሆኑት ዶክተር ወርቅነህ፤ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ሀገራችንን በውጭ ግንኙነት ዘርፍ እንድትታወቅ ያደረጉም የለውጥ አራማጅ ናቸው። ለለውጡ ስኬታማነትም በመስሪያ ቤታቸው ውስጥ ስር ነቀል የሪፎርም ተግባር የከወኑ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል።

እናም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጥላቻ ምልከታና በሌሎች “ቹ!” ባይነት እየተመሩ የሰዎችን መልካም ስምና ዝና ለማጥፋት መሞከር ነውረኛ ተግባር መሆኑን የአሉባልተኞች ልሳን የሆነው ሹክሹክታ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል። በምንደኛነት ተሰልፎ ለለውጥ የሚተጉ ሰዎች ላይ ያልተገባና ከማነነታቸው ጋር አብሮ የማይሄድ ፀያፍ ስምን በአሉባልታ መለጠፍ፤ የፀረ ለውጥ ኃይሎች አባሪና ተባባሪ ከመባል የሚያድን አለመሆኑንም ህሊና እንዳለው ፍጡር ሰክኖ መረዳት ይኖርበታል እላለሁ። አበቃሁ። ሰናይ ጊዜ።