Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹ቅድሚያ መከናወን የሚገባቸው ተግባራት ሳይጠናቀቁ ወደምርጫ መግባት ለውጡን መቀልበስ ይሆናል››-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር

0 1,024

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግሥት በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት ከሚሰራባቸው ዘርፎች ዋነኛው የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጎልበት ነው፡፡ በዚህም ከጥቂት ወራት አስቀድሞ በመንግሥት በተደረገ ጥሪ ከአገር ውጭ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር እንደገቡ ይታወቃል፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄም ጥሪውን ተቀብሎ ከገቡት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ እኛም ለዛሬ ከንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች፣ ቀጣይ ምርጫና የንቅናቄው ቁመናና ተግባራት ላይ አተኩረን ያደረግነውን ቆይታ እነሆ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄን በተመለከተ በአንድ በኩል ለሁለት እንደተከፈለ በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ አንድነት ውስጥ እንዳለ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ቁመና ከእነዚህ ሁለት ሃሳቦች በየትኛው ላይ ያርፋል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ማንኛውም ግለሰብ ከአባልነት እንደወጣ ሊገልጽ ይችላል፡፡ አንድና ሁለት ሰው መውጣቱን መግለጹም የሚቀይረው ነገር አይኖርም፡፡ ይልቁንም ድርጅቱ በጉባዔው የወሰናቸውን ውሳኔዎች የማስፈፀም ኃላፊነት ያለው በመሆኑም በጉባዔ ደረጃ ወስኖ ከንቅናቄነት ወደ ፓርቲነት እንዲቀየር ወስኗል፡፡ ፓርቲ የማቋቋም ኃላፊነት የሚመለከታቸው የተለያዩ ግብረ ኃይሎች አቋቁሞ እንዲሠሩ ኃላፊነት ሰጥቶ በዛ መሠረት ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመንግሥት ጥሪ ትግል ለማድረግ ወደ አገር ከገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ አርበኞች ግንቦት ሰባት ነው፡፡ ለመሆኑ ወደ አገር ከገባችሁ በኋላ  ምን ምን ተግባራትን አከናወናችሁ? 

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- አርበኞች ግንቦት ሰባት በዋናነት ሦስት ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሲሠራ ነበር፡ ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ አስቀድሞም አስቸኳይ ጉባዔ ጠርቶ ከፊቱ ያሉ ሥራዎች ምን እንደሆኑ ለይቶ አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ከንቅናቄነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት መቀየርና ለዚህ የሚያስፈልጉትን የድርጅት ሥራዎችን ማከናወን ይገኝበታል፡፡ ወደ አገር ከገባ በኋላም አንዱና ዋነኛው 90 በመቶ በላይ ሥራው በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ለአዲሱ ፓርቲ መሠረት የሚሆኑ በምርጫ ወረዳ ላይ ያተኮረ የድርጅት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ለአዲሱ ፓርቲ መሠረት በሚሆን መልኩም በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ በሰሜኑ በአማራ ክልል፣ በደቡብ በሁሉም ቦታዎች፣ በተወሰኑ ኦሮሚያ አካባቢዎች፣ በአዲስ አበባ እንዲሁም በሐረርና ድሬዳዋ መሠረታዊ ድርጅት አካሎቹን እያቋቋመ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ በአፋርና በጋምቤላ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመሥራት የሚያስችል መዋቅሮች እየተዘረጉ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት አዲሱ ፓርቲ እንዲቋቋም እየተሠራ በመሆኑ ለዚህ ታሳቢ ተደርጎም እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከሌሎች አብረው ለመሥራት ከሚሹ ድርጅቶች ጋር በምን መልኩ ይኬድበት? የሚለው በማስቀመጥ በጋራ ለመሥራት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡

ከህብረተሰቡ ጋር በሚደረጉ ስብሰባዎች የድርጅቱን አቋሞች የማስተዋወቅ ሥራም ወደ አገር ከተገባ በኋላ በስፋት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለውጡ የታለመለትን ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመመስረት ሥራ ላይ ከለውጡ ኃይሎች ጋር በመሆን ለውጡ በምንም ዓይነት መልኩ እንዳይቀለበስና የታለመለት ቦታ እንዲደርስ ባለው አቅም ሁሉ እያገዘ ሲሆን፤ ከመንግሥት ጋርም ለመሥራት እየተሞከረ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምርጫ ቦርድ ወደ አገር ከገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ምዝገባ ያከናወኑት እጅጉን አናሳ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አርበኞች ግንቦት ሰባት ምዝገባ አካሂዶ በሕጋዊ መንገድ እንቅስቃሴውን ጀምሯል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የአርበኞች ግንቦት ሰባት ፓርቲ ሊሆን መንገድ ጀምሯል፡፡ በመሆኑም አንዴ ተመዝግቦ ዳግም በሁለትና በሦስት ወር ውስጥ ዳግም ፓርቲው ሲመሰረት ከመመዝገብ የሚመሠረተውን አዲስ ፓርቲ ማስመዝገብ ይሻላል የሚል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚገባ ይህን ለማድረግ መመዝገቡ ወሳኝ እንደሆነም ያምናል፡፡ በመሆኑም ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ምዝገባውን ያካሂዳል፡፡ ይህንንም ምርጫ ቦርድ ያውቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ በቁጥር ከፍተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውህደት እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ አርበኞች ግንቦት ሰባት ተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ያለ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለእናንተ የውህደቱ መነሻ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በወቅቱ በንቅናቄነት ሲመሰረት የነበረውን ሥርዓት ለመጣልና ለማዳከም የሚሠሩ ሥራዎችን ለማከናወን በሁለት ጉዳዮች ላይ ነበር ስብሰብ የተደረገው፡፡ ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር መሥራት አንዱ ሲሆን፤ የአገር አንድነት እንዲከበር ማድረግ ደግሞ ሌላኛው ነበር፡፡ ይህ አንዱ ጥቅሙ ለውጥ የሚፈልገው ኃይል በአስተሳሰብ እንዳይለያይ አንድ ላይ ሆኖ ለውጡ እስኪመጣ ድረስ እንዲሄድ ለማድረግ ያስችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከንቅናቄነት ወደ ፓርቲነት እንዲቀየር መወሰኑ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ውህደት ለመፍጠር መታሰቡ ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ነው፡፡

ከንቅናቄነት ወደ ፓርቲነት ሲቀየር ተወዳድሮ የሥልጣን ፉክክር ሊያደረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዝርዝር ፖሊሲ ማውጣት ይጠይቃል፡፡ ለፖሊሲውም የርዕዮተ ዓለም ቅኝት ምን እንደሆነ መስማማት ይገባል፡፡ በዚህ መሠረትም አስቸኳይ ጉባዔ በተደረገበት ወቅት ሁለት መሠረታዊ አመለካከቶች የሚገዙት ዝርዝር ፖሊሲዎች እንዲወጡ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንዱ የሚካተት አመለካከት ነው፡፡ በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ደግሞ የማህበራዊ ፍትሕ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ እንዲካተት ማድረግ ይሆናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ደሃ፣ በርካታ ሥራ አጥ ያለበት፣ ብዙ አረጋውያንና ህጻናት እንዲሁም ራሳቸውን ያልቻሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ባሉበት አገር ዝም ብሎ ነገሮችን ወደ ገበያው መልቀቅ ሳይሆን ገበያው ያለውን አቅም ለይቶ ከመጠቀም አንፃር መሠራት እንዳለበት ይታመናል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ውጪ ለዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በሂደቱ ውስጥ በቀዳዳው ላይ ለሚወድቁ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያስብ የመንግሥት ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማሳካትም ማህበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ይታገላል፡፡ እነዚህ ሁለት መሠረታዊ አመለካከቶች በመያዝ ዝርዝር ፖሊሲ እንዲወጣ ጉባዔው መመሪያውን ለግብረ ኃይሉ ሰጥቷል፡፡

ግብረኃይሉ መመሪያውን ተቀብሎ ዝርዝር ፖሊሲዎችን እየሠራ ሲሆን፤ በቅርቡም ይጠናቀቃሉ፡፡ በዛ ላይ ተመስርቶ ዴሞክራሲያዊ የዜግነት ፖለቲካ እንዲሁም ማህበራዊ ፍትሕ እንደ ርዕዮተ ዓለም ቅኝት የሚያቀነቅኑ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ወስኗል፡፡ ይህ ሲደረግም በአደረጃጀት ደረጃ በምን መልኩ ይሠራል? ውህደት ሲፈጠርስ እንዴት ነው? የሚሉ አንኳር ጉዳዮችን አብሮ ይመለከታል፡፡

በአገሪቱ ከዚህ ቀደም የተለመደው ከታች ከህብረተሰቡ የተነሳ ሰፊ መሠረት ያለው የፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡ ጥምረትም ሆነ ውህደት ሲፈጠር በላይ ያሉ አመራሮች ተነጋግረው የሚፈጥሩት ነው፡፡ ይህን መሰል አካሄድ ከአሁን በኋላ መኖር እንደሌለበትም ታምኗል፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትም አዲስ በሚፈጠረው ፓርቲ አመራሮች ወደ ወረዳዎች ወርደው የፓርቲው አባላት ወደ ጉባዔው መሄድ ያለበትን መምረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎችም ጋር ውህደት ሲፈጠር አባላት በሙሉ ወረዳው ላይ ይሰበሰባሉ፡፡ የወረዳውንም መሪዎች ይመርጣሉ፡፡ በዚህም ለወረዳው የሚወዳደሩትን ለወረዳው ወደ ጉባዔ የሚሄዱትን የሚመርጡት እታች ያለው መዋቅር ይሆናል፡፡ ይህም ማንም ከላይ ሆኖ የሚወስንበትን አካሄድ ያስቀራል፡፡ በዚህ መልኩ ለመጓዝ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ጋርም ስምምነት ተፈጥሮ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በቀጣይም በዚህ መልኩ ለመጓዝ ፍላጎት ላለው ለማንኛውም ፓርቲ በሩ ክፍት ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቀጣይ 2012 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ያላችሁ አስተያየት ምንድን ነው? እያደረጋችሁ ያላችሁትስ ዝግጅት ምን ይመስላል? ለህዝቡስ ምን ይዛችሁ መጥታችኋል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ከውህደቱ ባሻገር የፓርቲውን መሠረት መጣል እንዲሁም አባላት ማሰባሰብ በአሁኑ ወቅት እየተሠራበት ነው፡፡ የለውጡ ዋነኛ ዓላማ ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ በነበሩ የምርጫ ሂደቶች ኢህአዴግም መቶ በመቶ እንዳሸነፈ ሲገልፅ ነበር፡፡ በመሆኑም በ2012 የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ እንዲህ ዓይነት የውሸትና የለበጣ ምርጫ ሳይሆን ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መፍጠር ከሆነ ለዚህ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ፓርቲው ያምናል፡፡

ቀዳሚ ሥራዎች መካከልም ሰላም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ይህን ለማመቻቸት መሥራት ሊሆን ይገባል፡፡ ማንም ሰው በፈለገው ቦታ ሄዶ በነፃነት ማደራጀት፣ ማንም ማንንም የማያስፈራራበት ሃሳቦች ብቻ ለህብረተሰቡ ቀርበው ህዝብ ያዋጣኛል ያለውን የሚመርጥበት አካባቢ በደንብ ካልተፈጠረና ምርጫው ዕውነትም ፍትሐዊ ነው የሚባል ካልሆነ አገሪቱ ተመልሳ የነበረችበት ማጥ ውስጥ እንደሚገባ አያጠራጥርም፡፡ ከአሁን በኋላ ህዝብ የነበረው ዓይነት አምባገነንነትና የተበላሸ ሥርዓትን መሸከም አይችልም፡፡ በመሆኑም ችግሩ ከተፈጠረ እንደከዚህ በፊቱ ሳይሆን የዚህች አገር መኖር ራሱ በጥያቄ ውስጥ የሚከት ይሆናል፡፡

ምርጫውን ዕውነተኛ ፍትሐዊ የህዝብ ፍላጎት መገለጫ መሆኑን ማረጋገጥ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በመሆኑም ምርጫው በ2012 ዓ.ም ይደረጋል ስለተባለ ከዚህ ቀደም የነበረው ሥርዓት በዛ ቀጥሏልና በዛው ቀን መሆን አለበት መባል አይኖርበትም፡፡ ዕውነተኛ ምርጫ ለማድረግ መሻሻል ያለባቸው ሕጎች ካሉ ተሻሽለው ተቋማቶችም በተመሳሳይ ማሻሻል ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

በአሁኑ ወቅት ትልቁ ችግር የሆነው በየክልሉ የፌደራል መንግስት የማይቆጣጠራቸው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ጦሮች በየክልሉ መኖር ነው፡፡ እነዚህ ታዛዥነታቸው ለክልሉ የሆኑ ኃይሎች አንድ ድርጅት ወደዛ ሄዶ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢፈልግ እንኳ ጦር የያዙ ሰዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ አይታወቅም፡፡ በመሆኑም እነዚህና መሠል ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ሳይበጅላቸውና ሳይረጋገጡ ምርጫ ማድረግ አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ መክተት ይሆናል፡፡ ስለሆነም በዚህ ቀን ይደረጋል ብሎ አጥር ከማበጀት መሠራት ያለባቸውን የቅድሚያ ተግባራት ተተግብረዋል ወይ? የሚለው በቅድሚያ መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ ሥራዎቹም በወቅቱ ከተጠናቀቁና ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል ንጹህ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ከተባለ ይደረጋል፡፡ አልያ ግን ምርጫ መደረግ አለበት በሚል ብቻ ቅድሚያ መከናወን የሚገባቸው ተግባራት ሳይጠናቀቁ ወደዛ ማምራት እጅጉን መጥፎና ለውጥም መቀልበስ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥት የያዘው የአመራር ሂደት አገሪቱን ወደየት ይወስዳታል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- በተለይ የለውጥ ኃይል የሚባለው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው ኃይል አገሪቱን ወደ ዕውነተኛ ዴሞክራያዊ ሥርዓት መውሰድ እንደሚፈልግ እየገለጸ ነው፡፡ የሚወሰዱት እርምጃዎች፣ ሕጎችን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት፣ እስረኞችን መፍታት እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ መንግሥት ከልቡ ለለውጥ ፍላጎት እንዳላው ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉ ነገር ይሳካል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ በቀድሞ ፓርቲ ውስጥ ያለ ሁሉ ይህን ይደግፋል ማለትም አይደለም፡፡ እየተወረደ ሲኬድ በጣም ብዙ እንቅፋት የሚፈጥሩ ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት ይኖራሉ፡፡

ለውጡን የሚመሩት በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ኃይሎች በእርግጥም ይህን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ነው ለውጡ የታለመለት ግብ እንዲደርስ ድጋፍ የሚደረገው፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ልዩነት ካለም ውድድር የሚደረገው ከዛ በኋላ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የፖለቲካ ኃይሎች ነን የሚሉት ዋና ኃላፊነት ይኼ ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር ተጋግዞ ለውጡን ከዳር  ማድረስ ነው፡፡ አሁን የመወዳደሪያና የመጣያ ጊዜም እንዳልሆነ ማወቅ ይገባል፡፡ የመንግሥት የለውጥ ኃይሎች ተባሮ ለለውጥ መስራቱን እንደሚፈልጉ ዕምነት ተጥሎባቸዋል የቅርብ ክትትልም በሥራቸው ላይ ይደረጋል፡፡ ችግር አለ ተብሎ ከታሰበም መንገድ ተፈልጎ ይነገራቸዋል፡፡ የተሻለ መንገድ የተባለውንም አማራጭ ሃሳብ ይቀርባል፡፡ ሂደቱንም በተሻለ መንገድ በመውሰድ ለፉክክር የሚያደርሰውን መንገድ የመዘርጋት ሥራ ይሰራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሂደቱ ውስጥ መቀጠል ያለበት ጥንካሬና መስተካከል ያለበት ድክመትስ ይኖር ይሆን?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ከበፊቱ ሥርዓት የተወረሱ ያልተላቀቁ ሃሳቦች አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ በየክልሉ ያሉ አመለካከቶች እንዲሁም በየክልሉ ጎረምሶች እንደፈለጉ እንደሚያደርጉ ሲናገሩና ሲበጠብጡም ይስተዋላል፡፡ በተያያዘ ከ10 እስከ 20 ሺህ የሚደርስ ትልቅ ኃይል ይዘው ማን ይነካናል? የሚሉ፣ ወንጀለኛ እየደበቁ ያሉም አሉ፡፡ እነኚህ ሁሉ ጉዳዮች መሻሻል ያለባቸው ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ አልቋል የሚባለው መዳረሻ ለሆነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መምጣት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሲያልቁም ነው፡፡ በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት ገና ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው 2012 አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ለማመቻቸት አይበቃም በሚል ነው የሚነሳው፡፡

በሌላ በኩል የሕጎች መሻሻል፣ በነፃነት መነጋገር መጀመሩ እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን የመንግሥትን ፕሮፖጋንዳ ከመለፈፍ ወጥተው ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እየሠሩ መታየታቸው ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ምንም እንኳ በአቅም የሚስተዋሉ ውስንነቶች እንዳሉ ቢታይም ልዩነቶችን በመነጋገር በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ከስምምነት እስከተደረሰ ድረስ እነኚህ ሁሉ መፍትሔ ይኖራቸዋል፡፡ በየክልሉ ያሉ ግጭት የሚፈጥሩ አካላነት በቶሎ መግታት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ስምምነት መድረስና ከዚህ በኋላ ሃሳቡን ለህዝብ በማቅረብ የመወሰን ሥልጣንን ለህዝብ መተው ያስፈልጋል፡፡  ይህ ሁሉ ማድረግ ከተቻለ መሻሻል ያለባቸው ሕጎች ተቋማት እንዲሁም ደንቦች ከተሻሻሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ይቻላል፡፡ ይህም ትልቅ ድል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉትን ግጭትና አለመረጋጋቶች ለማቃለል መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ከህዝቡ ምን ይጠበቃል?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ችግሮችን ለመፍታትና አዲስ ሥርዓት የመፍጠር ኃላፊነት ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የመንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ከህዝቡ የሚጠበቁ ሥራዎች አሉ፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ስምምነት መፍጠር ከዚህ በፊት በነበረው ዓይነት የለበጣ የማጭበርበርና የሴራ ፖለቲካ ለመውጣት ያግዛል፡፡ ሃሳብ ለህብረተሰቡ የሚቀርብበት፣ የትም ቦታ ያለምንም እንቅፋት የሚደረስበትና ህዝቡ በነፃነት ሊመርጥ የሚችልበትን መንገድ ላይ መስማማትና ለዛም መንገዱን መጥረግ ያስፈልጋል፡፡ ከመንግሥት በኩል ስምምነቶች ከተደረሱ በኋላ መንግሥት እንደ ብቸኛው ሕጋዊ ጉልበት የመጠቀም መብት ያለው አካል ሲሆንም ግጭቶችን አለመረጋጋቶችን በቀላሉ ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን የማስተካከል ኃላፊነትም አለበት፡፡ መቀየር ያለባቸው ሕጎች ሲኖሩ ተመካክሮና ተነጋሮ በምን መልኩ ሊቀየር እንደሚገባ በመወያት ሊሠራ፣ የዳኝነት ሥርዓቱ ገና ሊሻሻል ይገባዋል፡፡ በተመሳሳይ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ቀደም ብሎ የአንድ ፓርቲ መጠቀሚያ ነበሩ፡፡ አሁን ከዛ ወጥተው ማህበረሰቡን የሚያገለግሉ ከምንም የፖለቲካ ኃይሎች ነፃ መሆን አለባቸው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በቁጥር ከመብዛት ሰብሰብ በማለት ትርጉም ያለው በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ፓርቲ መመስረት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ህብረተሰቡም ከዚህ በፊት ከነበረው ከስሜትና ከንዴት እንዲሁም ከቂም በቀል ወጥቶ የሚመጣውን ስርዓት ለመቀበል የባህሪ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ህዝቡ የሞራል መሠረቱ ክፉኛ ተናግቷል፡፡ ከቤተዕምነቶች ጀምሮ በየቦታው ጉቦ የሚሰጥበት እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ተማሪና አስተማሪ ጫት እየተቃመ የሚያወራበት አገር ችግርን ማስተካከል ረጅም ጊዜን ይወስዳል፡፡

በዚህ መልኩ ወደየት እንደሚኬድ ከታወቀ፣ በነፃነት መወያየት ከተቻለ፣ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዓላማ መነሻ አድርገው መሥራት ከቻሉና ከተባበሩ፣ በየሃይማኖቱ ግብረገብ ማስተማር ከተቻለ፣ ጨዋነት ላይ ከተሠራ፣ ትምህርት ቤቶች ጤነኛ ዜጎች ማፍራት የሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ ከገቡ ችግሮችን ለመፍታት አያዳግትም፡፡ በተያያዘ የፖለቲካ ድርጅቶች ለፖለቲካ ሥልጣን የሚወዳደሩት አገር ለማገልገል እንጂ ከመቼው ስልጣን ላይ ወጥቶ ለመስረቅ እንዳልሆነ የሚያምኑበት፣ ህብረተሰቡም ማነው ለዕውነት የሚያገለግለው? ማንስ ነው? ይህችን አገር በጋራ ወደፊት ሊወስድ የሚችለው? እያለ ማሰብ የሚችልበት ሁኔታ ሲደረስ የተረጋጋ ማህበረሰብን መፍጠር ይቻላል፡፡ ህብረተሰቡ ጭቆና ውስጥ የነበር፡፡ በግፍ ውስጥ ሲፈራ የኖረ አሁንም ፍርሃቱ ያለቀቀው በመሆኑ ለውጡ ይቀለበስ ይሆን? የሚል ስጋት ውስጥ የሚታየውም በእነዚሁ ችግሮች በመሆኑ ከዚህ ሁሉ መውጣት ይኖርበታል፡፡  ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ትብብር ይፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለም ሰፊ ታሪክና የረጅም ጊዜ ስልጣኔ እንዳለው ለሚያወሳ ህዝብ የሚመጥን ስርዓትን መፍጠር ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ መከላከያ ሪፎርም እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም የብሔር ማመጣጠን፣ የዕዝ መቀነስ እጩ መኮንኖችን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መመልመል ያካትታልና እነዚህንና መሰል በተቋሙ እየተወሰዱ ያሉ ማሻሻያዎችን እንዴት ይመለከታቸዋል? በስጋት የሚነሳ ችግርስ አለ ወይ?

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- መከላከያ ለአንድ አገር በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ከሚባሉ ተቋማት ውስጥ ተጠቃሹ ነው፡፡ ሁሉንም በጋራ ሚጠብቀው ይኸው ኃይል ነው፡፡ ድንበር ብቻ ሳይሆን ሰላምንም የሚያረጋግጠውም ተቋሙ ነው፡፡ በመሆኑም አገሩን ለመጠበቅ የሚችል በብቃት ላይ የተመሠረተ በቂ ሥልጠና ያለው፣ በመሳሪያ የተደራጀና ችሎታ ያለው ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተመሳሳይ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቋሙ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ አንድን የፖለቲካ ቡድን ለማገዝ ወይንም ለመጥቀም ሳይሆን እንደ አገር የሚጠብቅ ተቋም ነው፡፡

ለ27 ዓመታት መከላከያ የአንድ ፓርቲ መሳሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሹመት የሚካሄደው ባለው የፓርቲ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከፓርቲም በላይ በተወሰነ ብሄር ላይ ትኩረት የተሰጠበት ሁኔታም ይስተዋልበት ነበር፡፡ በመሆኑም ይሄ መቀየር አለበት፡፡ መከላከያው ዕውነተኛ ሚናውን እንዲጫወትና ብቃት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ከፖለቲካ ወገንተኛነት የራቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በትምህርት፣ በዕውቀት የበለፀገ፣ ደረጃ በደረጃ እያደገ የራሱ የውስጥ ጠንካራ ባህል ያለው፣ ነፃነቱንና አገሩን የሚጠብቅ፣ አገሩን የሚወድ እና ለአገሩ የቆመ ሠራዊት ማድረግ ይገባል፡፡ ይሄም ጊዜ የሚወስድ ሥራ ነው፡፡ እንዲህ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ይህን ተቋም መቀየር ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑም ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ጅማሮ ጥሩ በመሆኑም ተጠናክሮና መሠረት ይዞ መገንባት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም በመከላከያ ውስጥ የሚሠሩትም ሆኑ መንግሥት ተባብረው እንደሚሰሩ ዕምነት አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሁሉም የሚሆን መከለከያ ከተቋቋመም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ይኖረዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቃለምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– እኔም አመሰግናለሁ!

አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011

በፍዮሪ ተወልደ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy