NEWS

‹‹በምህረት አዋጁ የተፈቱ ታራሚዎች ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉበት መንገድ መመቻቸት አለበት›› አቶ ዘለቀ ዳላሎ የፌዴራል የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

By Admin

January 30, 2019

አዲስ አበባ፡- መንግሥት በምህረት አዋጁ የተፈቱ ታራሚዎች ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን  መንገድ ማመቻቸት እንዳለበት የፌዴራል የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ፡፡

የፌዴራል የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዳላሎ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት፤ በምህረት አዋጁ ከተፈቱት ሰዎች ውስጥ የዕድሜ ልክ እስራትና ሞት የተፈረደባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከልም ለብዙ ዓመታት የታሰሩ አሉባቸው፡፡ ለብዙ ዓመታት በሽብር የታሰረን ሰው ወደ ማኅበረሰቡ ስትቀላቅለው አቀባበሉ ከባድ ነው፡፡ ቢሮ ድረስ በመምጣት ከማኅበረሰቡ ጋር እንዴት ነው የምንቀላቀለው የሚሉ ጥያቄዎች ያነሱም  ነበሩ፡፡  ስለሆነም መንግሥት አንድ ታራሚ ሲፈታ ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀልበትን ሁኔታ በማማቻቸት ረገድ የተጠናከረ ሥራ ማከናወን አለበት፡፡

እንደ አቶ ዘለቀ ዳላሎ ገለጻ፤ አሁን መንግሥት ከአቅም አንጻር ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ እነዚህን ሰዎች ፈትቶ መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ አቅጣጫ ማሳየትና ማስተማር ያስፈልግ ነበር፡፡ የተሰራው ሥራ መልካም ቢሆንም ለሰዎቹ ነጸነት መስጠት እንጂ በቀጣይ ማድረግ ስለሚገባቸው ትኩረት አለመሰጠቱ አንዱ ችግር ነው፡፡

ከፌዴራል የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የምህረት አዋጁ ተግባራዊ የሆነው ከሐምሌ 13 ቀን 2010 እስከ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ጊዜም በአምስት ወር ውስጥ ብቻ ከሶማሌ፣ ከአፋርና ከጋምቤላ ክልሎች ውጭ ከ13ሺ በላይ ዜጎች በምህረት አዋጁ መሰረት ጥያቄ አቅርበው የምህረት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ጥሪ ስለተደረገ ሪፖርቱ ገና በሂደት ላይ ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡

ከፌዴራል የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዳላሎ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በገጽ 11 ይመልከቱ፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 22/2011

አጎናፍር ገዛኸኝ