NEWS

በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር የሚገኘው የሁመራ ኦምነሐጀር መንገድ ተከፈተ

By Admin

January 08, 2019

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚያገናኘውን የሁመራ ኦምነሐጀር መንገድ ዛሬ በይፋ ከፈቱ።

ኡምናሀጅር-ሁመራ ድንበር መከፈት በሁለቱ ወገን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የበለጠ ከማዳበሩ በተጨማሪ በረጅም ጊዜ የድንበር ተሻጋሪ የንግድ እንቅስቃሴን እንደሚያቀላጥፍ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

መንገዱን በይፋ ሥራ ለማስጀመር ዛሬ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ሁመራ – ኦምነሐጀር መገኛ ላይ ደማቅ ስነ-ሰርዓት ተከናውኗል።

በስነ-ስርዓቱ ላይም የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፣ የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ጀነራል  ሳህረ መኮንንና የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

በሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ለመሪዎቹ ደማቅ አቀባበል አድርገዋል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው ይህ መንገድን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዝግ ሆነው ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በወሰዳቸው የተለያዩ አርምጃዎች ሳቢያ በአሁኑ ወቅት የአገራቱ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት እየተመለሰ ነው።

ከኤርትራዋ ርእሰ መዲና 500 ኪሎ ሜተር በላይ ርቀት ላይ የሚገኘው የሁመራ ኦምነሐጀር መንገድ መከፈትም የዚሁ ጥረት አካል ነው።

ሁለቱን አገሮች በሚያዋስነው በዚህ የድንበር አካባቢ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደቀድሞው ሁኔታ ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት አካል እንደሆነም ተመልክቷል።

ከወራት በፊት አገራቱ የወደብ አገልግሎትን ለማስጀመረ መስማማታቸውም ይታወሳል።

መንገዱ ኢትዮጵያ በዋነኝነት ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው የቅባት እህሎች በስፋት የሚመረቱበት ሁመራ  አካባቢ የሚገኝ ነው።

የመንገዱ  መከፈት  የኤርትራና ኢትዮጵያ  ወንድማማች ህዝቦችን ግንኙነት  እንደሚያጠናከረው በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ የአገሮቹ ዜጎች በስፍራው ለተገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ገልፀዋል፡፡