ከሳውዲ አረቢያ ጋር በተደረገው የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት በህጋዊ መንገድ ለሚሄዱ ሰራተኞች የቪዛ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ይርጋለም እንዳስታወቁት ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ለሚመጡት ህጋዊ ተጓዦች የሳውዲ አረቢያ ኢምባሲ በትላንትናው ዕለት የቪዛ አገልግሎ መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ ፣8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ፣በሚሄዱበት የስራ መስክ ስልጠና ወስደው የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ፣ የጤና ኢንሹራንስ የተገባላቸው፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ያደረጉና ከወንጀል ነጻ የሆኑ ሰራተኞች በአስቀጣሪ ኤጀንሲ በኩል ቪዛውን አግኝተው መሄድ እንደሚችሉ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በፊት የውጭ ሀገር ሰርተው የተመለሱና መረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ግን ስልጠናውን ለመውሰድ አይገደዱም፤ የብቃት ማረጋገጫ ግን ይወስዳሉም ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ሰራተኞች ወደ ሳውዲ ሲሄዱ መብቶቻቸውን የሚያስጠብቁ አዳዲስ ስምምነቶች መደረጋቸውንም አቶ አስፋው ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለስራ በሄዱበት አካባቢም የአካል ጉዳት ወይም በስራ ላይ እያሉ ሞት ቢያግጥም ኢንሹራንስ ተገብቶላቸው እንዲሄዱም ገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት ወደ ሳውዲ የሄዱ ሰራተኞች ስልክ የማያገኙበት አጋጣሚ ነበር ያሉት አቶ አስፋው ፣አሁን ላይ የስልክ አገልግሎትም እንዲያገኙ ስምምነት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
የሰራተኛና የአሰሪ ግንኙነቱን የተሻለ ለማድረግ በኮምፒውተር በታገዘ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ደመወዝ መከፈል አለመከፈሉን የሚያረጋግጥ ስርዓትም ተዘርግቷል ተብሏል፡፡በዚህም በአሰሪው በኩል ቅጣት የሚያስከትል የቁጥጥር ስርዓት መኖሩ ተመልክቷል፡፡
ከ200 በላይ የሚሆኑ ህጋዊ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ወስደው ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር በመስራት እንሆኑም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በቅርቡ ከሳውዲ አረቢያ ጋር በተደረገው ስምምንት ወደ አገሪቱ ለስራ የሚያመሩ ኢትዮጵያዊያን ዝቅተኛው ክፍያ 1ሺህ የሳውዲ ሪያል እንዲሆን ከስምምነት መደረሱም ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡