Politics

የትግራይ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ ሊረበሽ አይገባም—ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

By Admin

January 08, 2019

የትግራይ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ ሊረበሽ አይገባም—ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

(ኢ.ፕ.ድ)

የትግራይ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ሳይረበሽ በልማቱ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ህጋዊና ኃላፊነቱንም ለመወጣት የሚያስችል ነው።

በመሆኑም የክልሉ ህዝብ ይሄንን ተገንዝቦ ያለምንም መረበሽ የልማት ስራውን በተረጋጋ መልኩ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

ህዝቡ የሚያነሳው የህገ-መንግስት ይከበርልን ጥያቄ እራሱ ከማክበር የሚጀምር መሆኑንም ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር በመግለጫቸው አመልክተዋል።

የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማስከበርን ጉዳይም ህዝቡ በፈጠረው አደረጃጀት አንድነቱን ማስቀጠል እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ባደረጉት የጋራ ስምምነት የሁመራ ኦምሃጅር መንገድ መከፈትም ለሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ጠቃሚ እንደሆነ ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ መንገዱ የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማሳደግ ባለፈው ቀጣይ ህጋዊ መስመር ለማስያዝም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።