Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በቀላሉ አይታይም›› -ዶክተር አምባቸው መኮንን የጠ/ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ

0 3,742

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‹‹የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ህዝብ እየሞተበት ያለ ጥያቄ እንደመሆኑ በቀላሉ የሚታይ አይደለም›› ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ  ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን አስታወቁ፡፡  ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትነት መታጨታቸውን ህዝቡ ባለመፈለጉ በፖለቲካ ተሳትፏቸው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡

አማካሪ ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በወልቃይትና በራያ አካባቢ የሚታየው ችግር በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፣ ለአገሪቱም የሰላም መናጋት ምክንያት እየሆነ ያለ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ካልተፈታ ሁለቱ ክልሎችም ሆኑ አገሪቱ ሰላም አያገኙም፡፡

‹‹የወልቃይትና ራያ ጉዳይ እስካሁን ሲገፋ ቆይቷል፤ እንዳልታየና እንዳልተሰማም ሊታለፍ ተሞክሯል››ያሉት ዶክተር አምባቸው፣  ጉዳዩ በአሁኑ ወቅት  ሊታለፍ የሚያስችል ደረጃና ወቅት ላይ አለመሆኑን የአዴፓ ግምገማ ማመላከቱንም አስታውቀዋል፡፡

ይህ ጥያቄ መፈታት ያለበትና መያዝም ያለበትም በገለልተኛ አካል መሆኑን አመልክተው፤ ክልሎቹ እንዲሁም ሁለቱም ድርጅቶች እየተገፋፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን ለአገር ሰላምና ለህዝቦቹ ደህንነት እንዲሁም መብት ሲባል የፌዴራል መንግስት ሊይዘው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹በመሆኑም ጉዳዩን ደረጃ በደረጃ ተቋማዊ ባለቤት እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ ነው›› ያሉት ዶክተር አምባቸው፣ ስለዚህ የማንነትና የወሰን ጉዳዮችን የሚከታተል ኮሚሽን መቋቋምንም የዚህ ውጤት አድርገው እንደሚወስዱት ተናግረዋል፡፡

እንደ አማካሪ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ጉዳዩን በተመለከተ የሃሳብ ልዩነቶችም በስፋት ይታያሉ፡፡ በቀና መንገድ ያለመያዝ ነገሮችም ይስተዋላሉ፡፡

ጉዳዩ ቀላል የማይባል ውዝግብ ሊያስነሳ  እንደሚችል ጠቅሰው፣ብዙ መወያየትን እንዲሁም ብዙ መወዛገብንም ሊጠይቅ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

በቅርቡ የወሰንና ማንነት ጉዳዮችን በተመለከተ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መጽደቁን ጠቅሰው፣አዋጁ እንዳይጸድቅ  ተቃውሞ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ወደ እርቅና ሰላም በሚያመራው ጉዳይ ላይም እንዲሁ ጥርጥሬና ተቃውሞ እንደነበር አስታውዋል፡፡ የማንነት ጥያቄ ‹‹ቀረቡ ወይ አልቀረቡም›› የሚለውን በቅንነት ከማየት ይልቅ ጥያቄዎቹን የማጥፋትና እንዳልነበሩ የመቁጠር ነገሮች በፌዴራል ተቋማትም ጭምር እንደሚታዩ ገልፀዋል፡፡

‹‹ይህ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ በምንም ተዓምር ሊፈታው አይችልም›› ያሉት ዶክተር አምባቸው፣ከዚህም በጉዳዩ ላይ ያለው አመለካከት ምን ያህል የተዘባ መሆኑን መረዳት እንደሚቻል አስታውቀዋ ል፡፡ ጉዳዩን በመደበቅ መፍትሄ ሊመጣ እንደማይችልም አመልክተዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ ስለተደበቀ ነው ሊገድለን፤ ሊያጠፋን ከሚችል በሽታ  ደረጃ ላይ እየደረሰ ያለው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ጥያቄውን ህዝቡ በሚያነሳበት ልክ በግልጽ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ መፍትሄውንም እንዴት እናምጣ በሚለውም ላይ በጋራ መነጋገር እንደሚገባ፣ በመጠፋፋት ይህ አይነቱ በሽታ እንደማይጠፋም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ብዙ አፈና ተፈጽሟል፡፡ ሰዎችም ተጎሳቅለውበታል፤ ታስረውበታል፤ ተገርፈውበታል፡፡ ይህ የሚያስኬድ ቢሆን ኖሮ ይቻል ነበር›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ በመድረክ እያፈኑ በጉዳዩ ላይ ጥያቄ አልቀረበም፤ ወረቀት አልቀረበም ብሎ በመካድ ችግሩ ሊጠፋ አይችልም›› ያሉት ዶክተር አምባቸው፣ጉዳዩ መፍትሄ ካልተሰጠው ለአካባቢው፣ ለሁለቱም ክልሎችም ሆነ ለአገሪቱ የባሰ በሽታ የሚያመጣ መሆኑን በግላቸው እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶክተር አምባቸው ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትነት ታጭተው እንደነበር ጠቅሰው ፣ለህዝብ ፍላጎት ሲሉ ቦታውን መተዋቸውንና በፖለቲካ ተሳትፏቸው መቀጠላቸውን  ገልጸዋል፡፡

ዶክተር አምባቸው ለኢዴሪሪ ፕሬዚዳንትነት ታጭተው እንደነበር አስታውሰው፣ህዝቡ በፖለቲካ ተሳትፏቸው እንዲቀጥሉ በመፈለጉ የፕሬዚዳንትነት ስፍራውን መተዋቸውን ገልጸዋል፡፡

በካቢኔ ድልድል ወቅት እሳቸውን ለፕሬዚዳንትነት ቦታ በማሰብ ከካቢኔ ውጪ ተደርገው እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ እንዴት ይታሰባል የሚል አመለካከት በወቅቱ በተለያዩ መንገዶች መንጸባረቁን አስታውቀዋል፡፡

ዶክተር አምባቸው ወደ ፕሬዚዳንትነቱ ቦታ ያልመጡት ህዝቡ ባለመስማማቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ የፕሬዚዳ ንትነት ኃላፊነት  ትልቅ ስፍራ እንደሆነ እንደሚያምን በመጥቀስ፣ የፕሬዚዳንትነት ቦታው በሌላ ሰው ሊሸፈን  ይችላል የሚል እምነት ይዞ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡

ከዶክተር አምባቸው መኮንን ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በቅርቡ ለንባብ በምትበቃው የዘመን መጽሔት እትም ላይ ያገኙታል፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011

በአስቴር ኤልያስ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy