በ14 አገሮች በስድስት አህጉሮች እንዲሁም በአገራቸው ደግሞ በስድስት ግዛቶች በመዘዋወር ደም በመለገስ የሚታወቁት ሚስተር አርጁን ራሳድ ማናሊ የተባሉት አሜሪካዊ ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2011 ዓም በአዲስ አበባ በመገኘት ለ168ኛ ጊዜ ደም ለግሰዋል።
ሚስተር አርጁን ራሳድ ማናሊ በራሳቸው ተነሳሽነት ከአሜሪካ ድረስ በመምጣት ደም ከመለገስ ባሻገር የአገራችን ለበርካታ ጊዜ ደም የለገሱ ግለሰቦች የእውቅናና ሽልማት እንዲያገኙ መረሃ ግብር እንዲዘጋጅና በማድረግ ወጪውን ሙሉ ለሙሉ ሸፍነዋል።
በዚህ የዕውቅናና የሽልማት ስነስርዓት ላይ የጤና ሚኒስተሯ ወ/ሮ ሰሃራል አብዱላሂ እና የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሪክተር ዶክተር ሄሌና ሃይሉ በመገኘት ለፍተኛ የደም ለጋሾች ምስጋና አቅርበዋል የምስክር ወረቀትም አበርክተዋል።
ደም በመለገስ የምንጨምረው እንጂ የምንቀንሰው ህይወት የለም ያሉት የጤና ሚኒስትሯ በመኪና አደጋ፣ በወሊድና በሌሎች ምክንያቶች ዜጎች በደም እጦት ሳቢያ የሚያጋጥማቸውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ደም ልገሳ እያደረጉ ለሚገኙ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሪክተር ዶክተር ሄሌና ሃይሉ በበኩላቸው በአገራችን የበጎ ፈቃደኝነት ደም ልገሳ ከተጀመረ በኋላ የሚሰበሰበው የደም መጠን እየጨመረ በመሄዱ የብዙዎችን ህይወት መታደግ መቻሉን ገልጸዋል።
ዋና ዳይሪክተሯ እኚህ በጎ አድራጊ አሜሪካዊ ከአሜሪካ ድረስ በመምጣት ያደረጉት መልካም ነገር ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትምህርት ሊሆነን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በማኣረግ ገ/እግዚአብሄር