Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያዊያን የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች መከላከል ይችሉ ዘንድ በችግሮቻቸው ዙሪያ የመነጋገር ባህልን ሊያዳብሩ ይገባል ተባለ

0 1,049

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ መተማመንን በመገንባት የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በጋራ መከላከል ይችሉ ዘንድ በችግሮቻቸው ዙሪያ በግልፅ የመነጋገር ባህልን ማዳበር ግድ እንደሚላቸው የፖለቲካ መሪዎች ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ‘አዲስ ወግ’  በሚል ያዘጋጀውና ባለፈው አንድ አመት የአገሪቱ የለውጥ ሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎችን የዳሰሰ ውይይት ላለፉት ሁለት ቀናት በበሸራተን ሆቴል ተካሂዷል።

በዚሁ መድረክ ላይ ከተሳተፉት የፖለቲካ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና  የሲቪል ሶሳይቲ አባላት መካከል ሀሳባቸውን ለኢዜአ የሰጡ እንደተናገሩት የዚህ ዓይነቱን አገር አቀፍ መድረክ ህዝቡ በሚገጥሙት ፈተናዎችና የወደፊት ተስፋዎቹ ላይ ተነጋግሮ መፍትሄ ሊያመነጭበት የሚችል ባህል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል።

በአገር ጉዳይ ላይ የሚካሄዱት ይህንን የመሰሉት መስተጋብሮች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ሊወርዱ እንደሚገባም ነው  የውይይቱ ተሳታፊዎች ያሳሰቡት።

በምሁራንንና ፖለቲከኞችን ጨምሮ በዜጎች መካከል ገንቢ ውይይቶችን መልመድ በተለያየ መንገድ በህዝቡ ውስጥ የሚነሱ ኃሳቦችን፣ ጥያቄዎችንና ግርታዎችን ወደአዳራሽ በማምጣት ለችግሮች መፍትሄ በጋራ ለማፈላለግ አይነተኛ ሚና አለው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፤ የውይይት መድረኩ ስያሜ ራሱ አዲስ ወግ የሚል መሆኑ እና ንግግር መጀመሩ በራሱ ጥሩ ጅምር መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ይህ መድረክ በአይነቱ የመጀመሪያ ከመሆኑ አንፃር በበቂ ሁኔታ ኃሳብን ማንሸራሸር ያልተቻለበት በመሆኑ ጥልቅ ውይይት ማድረግ ይቻል ዘንድ ተመሳሳይ ውይይቶች እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ዘልቆ መለመድ መቻል አለበት ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ መላኩ ሙሉአለም  በበኩላቸው የሚሰሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ክፍተቱን ላያዩት ይችላሉ ሌላው ህብረተሰብ ግን ይሄን አላደረጋችሁም ይሄ ይቀራችኋል በሚል ማረሚያ ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ውይይት ባለበት ሁኔታ ግጭቶች በውይይት እየተፈቱ ስለሚሄዱ ብዙ ላይሰፉ ይችላሉ  ያሉት አቶ መላኩ ብዙ ቁም ነገሮች  ከመንግስት አካል፣ከሲቪክ ማህበራት፣ከተማሪዎች፣ ከምሁራን የተለያዩ ኃሳቦች የሚቀርብበት በመሆኑ ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኦዴግ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው ውይይቱ አገራዊ መግባባትን ለማሳካት ቀደም ብሎ መጀመር እንደነበረበት ገልፀው  በዚህ መልኩ  እየሰፋ ሁሉንም እያካተተ እንደሚሄድ አምናለሁ ብለዋል፡፡

“አገራዊ መግባባት ተቀራርቦ ከመነጋገር ነው የሚጀምረው “ያሉት የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር  አቶ አብርሃ ደስታ መነጋገር፣መቀራረብ እርስ በእርስ ለመተማመን እንደሚረዳ ተናግረዋል።

አገራዊ መግባባት ከመተማመን እንደሚጀምር ገልፀው “ውይይቱ መጠራጠሮችን በማስወገድ ለአገራችን እና ለህዝባችን  አገር ከሚከፋፍል ነገሮች ወጥተን በአገር ጉዳይ አንድ እንድንሆን ይጠቅመናል።” ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች ምንጫቸው ህዝብ ሳይሆን  የልሂቃኑ የልዩነት ኃሳቦች በመሆናቸው ይህን አስተሳሰብ ለመቀየር እና ለአገር እንድነት እና ብልጽግና በጋራ ለመስራት ይህ ውይይት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተናገሩት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy