NEWS

ሰላምና ዴሞክራሲን ጨምሮ የአስተዳደር ምሰሶዎች በሆኑ ስድስት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መርሃ ግብር ሊተገበር ነው

By Admin

March 04, 2019

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምና ዴሞክራሲን ጨምሮ የአስተዳደር ምሰሶዎች በሆኑ ስድስት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መርሃ ግብር ሊተገብር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዛሬ የደብረ ብርሃን ኢንደስትሪ ፓርክን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ መንግሥት በመጪዎቹ ዓመታት የአገሪቱን ህዳሴ ዳግም ለመቀስቀስ የሚያስችሉ ስድስት ምሰሶዎችን አዘጋጅቷል።

ምሰሶዎቹ ሠላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና፣ አንድነት፣ ፍትህና አገራዊ ኩራት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የመጀመሪያ ሠላም ነው፤ ሠላም ከሌለ አብሮ መኖር የለም፤ ሠላም ከሌለ አገር መገንባት የለም፤ ሠላም ከሌለ ወጥቶ መግባት ስለማይቻል” በሠላም ኢትዮጵያን እንገነባለን” ብለዋል።

አክለውም የአገሪቱ ህዝብ በኃይማኖት፣ በዘር፣ በአስተሳሰብ በርካታ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዓብይ በዚህ ረገድ ሁሉንም ማቀራረብ  የሚቻለው ዴሞክራሲን በማጠናከር በመሆኑ መንግስት በዚህም ላይ አትኩሮ እንደሚሰራ ተናገረዋል።

አገሪቱ በርካታ አንጡራ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤትና የተማረ የሰው ኃይል ስላላት ይህም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በማኅበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ፍትህ ማምጣት፣ አገራዊ አንድነትና ኩራትን ማረጋገጥ እንደ አራተኛ፣ አምስተኛና ስድስተኛ  ምሶሶ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እነዚህም ምሶሶዎች በቅርቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ ሆነው ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ይሁንና እነዚህን ምሶሶዎች ለመሥራት ከመንግሥትና ከሁሉም ዜጋ የላቀ ትጋት እንደሚጠይቅ ገልጸው በጋራ በመሥራት ስኬት ላይ መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ዜጎች የሕዝቡን አንድነት ለማናጋት የሚሰሩ ኃይሎችን መልዕክት በመዘንጋት በጋራ እንደ አገር ለመቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም በሕጻናት አዕምሮ ውስጥ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርና ሠላምን በመስበክ የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለ ማድረግ እንደሚገባና ለዛም መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።