Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የሚመጡ መንግስታት ኢትዮጵያ ከኔ በኋላም ትቀጥላለች ብለው ማመን አለባቸው”- አቶ ሌንጮ ለታ

0 970

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የሚመጡ መንግስታት ኢትዮጵያ ከኔ በኋላም ትቀጥላለች ብለው ማመን አለባቸው ሲሉ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት ትናንት በተካሄደው ‘አዲስ ወግ’  በተሰኘው ውይይት ላይ ባለፈው አንድ ዓመት የመጣውን ለውጥ ብሎም ያጋጠሙ ፈተናዎችን በዳሰሰው የውይይት መድረክ ላይ ነው አቶ ሌንጮ ይህንን ያሉት።

ከኦነግ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ ከጥቂት ዓመታት በፊት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተሰኘ ድርጅት መስርተዋል።

አቶ ሌንጮ በ ‘አዲስ ወግ’ ውይይት ላይ ያላቸውን የፖለቲካ ልምድና አቋም ለተወያዮች አካፍለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለው የፖለቲካ አሰላለፍ በብሄርና በአንድነት ላይ ባሉ ጫፎች የተዋቀረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ በአገራዊ ማንነት ላይ መስማማት አስፈላጊ መሆኑንና በኢትዮጵያ ግን በዚህ ሁኔታ ላይ ስምምነት እንደሌለም ጠቁመዋል አቶ ሌንጮ።

ለአብነትም “ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች፤ ኢትዮጵያዊነት ምን ምን ያካትታል?” የሚሉ ጽንስ ኃሳቦች ላይ ስምምነት ያለመኖሩን አብራርተዋል።

ይህ ባለበት ሁኔታ በአገሪቷ ያሉ የፖለቲካ አሰላለፎች ወደ ብሄርተኝነት ያደሉ መሆናቸውን ገለፃ አድርገዋል።

በኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች አገራት በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎች ያለመኖራቸውን በምሳሌነት ያነሱት አቶ ሌንጮ፤ በኢትዮጵያ ግን በርካታ ብሄርን መሰረት አድርገው የተደራጁ ፓርቲዎች መኖራቸውን አውስተዋል።

ለዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ ሁሉም ራሱን ሊጠይቅ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ሌንጮ፤ ለዚህ መልስ ካልተገኘ መፍትሄውን ማግኘት እንደማይቻልም ነው የተናገሩት።

መጪው ምርጫ ፍትሃዊና ነፃ እንዲሆን ለማድረግ የተቋማትና የአመለካካት ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን በምክረ ኃሳባቸው አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም የመጡ ገዥዎች በሙሉ “እኔ ከሌለው ኢትዮጵያ አትኖርም” የሚል እምነት አንግበው ይንቀሳቀሱ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሌንጮ፤ ይህ ከመነሻው የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑንና የሚመጡ መንግስታት ኢትዮጵያ ከእነሱ በኋላም እንደምትቀጥል ማመን አለባቸው ብለዋል።

እነዚህን ሁሉ አስተሳሰቦች ለመቀየርም ቀጣዩ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የፖለቲካ ልሂቃኑ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተቀራርበው መወያየት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy