Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህዝቦች መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር የሚደረገውን አፍራሽ እንቅስቃሴ መላው ህዝብ ሊታገለው ይገባል – የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት

0 1,069

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ልዩነትንና መከፋፈልን ለመፍጠር በተለያየ መንገድ የሚደረገውን አፍራሽ እንቅስቃሴ መላው ዜጋ በጋራ መታገል አለበት ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገረሳ ተናገሩ።

አቶ ለማ ይህንን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በተገኙበት ከቡኖ በደሌ ዞን ነዋሪዎች ጋር በበደሌ ከተማ ዛሬ በተካሄደው ውይይት ላይ ነው።

በዚሁ ወቅት አቶ ለማ የኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል፤ በአሁኑ ወቅትም አንድነቷን አስጠብቆ ለማቆየት ከሌሎች  ወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ ይሰራል ብለዋል።

“የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያን አንድነት የማስጠበቅ ግዴታ አለበት” ሲሉም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

በመሆኑም በህዝቦች መካከል ልዩነትንና መከፋፈልን ለመፍጠር በተለያየ መንገድ በተለያዩ አካላት የሚደረገውን አፍራሽ እንቅስቃሴ መላው ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በጋራ መታገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በዚሁ ወቅት የውይይቱ ተሳታፊዎች የመሰረተ ልማት፣ የሥራ አጥነትንና የጤና አገልግሎት እጥረትን ጨምሮ የተለያዩ የምጣኔ ኃብታዊና የፖለቲካ መብት ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የዞኑ ህዝብ ያሉበትን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሂደት ለመፍታት ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

በተለይም ህዝቡ ላለፉት ዓመታት ሲያቀርባቸው ለነበሩት የመልካም አስተዳደር፣ የፖለቲካ ነፃነትና ሌሎች የመብት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመላው ኦሮሚያ ያለውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ብቃት ለማሻሻል መንግስት ሰፊ ሥራ የጀመረ መሆኑን የተናገሩት አቶ ለማ የቡኖ በደሌ የጤና አገልገሎት ችግርም በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት ምላሽ እንደሚያገኝ አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት አገሪቱን ለመገንባት የተጀመረው  ጥረት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚሰማው አፍራሽ መልዕክት አይገታም ሲሉ ተናገረዋል።

በአገሪቱ ያለውን የህግ የበላይነት ለማጠናከር መንግስት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዓብይ ሆኖም ይህንን ጥረት በማደናቀፍ መንግስት የማይፈልገው የኃይል እርምጃ ውስጥ እንዲገባ ለሚገፋፉ ቡድኖች ምቹ መንገድ መፍጠር እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

አክለውም የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የሌለበት መሆኑን ጠቅሰው መላው ህዝብ በተለይም የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተፅእኖ የሚፈጥሩ የማህበረሰብ አባላት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ በትናንትናው እለት ከኢሉ አባቦራ ዞን ነዋሪዎች ጋርም ተመሳሳይ ውይይት አካሂደዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy