NEWS

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቃለ መሃላ ፈፀሙ

By Admin

April 26, 2019

በቅርቡ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 10 ቀን 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያቀረቧቸውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ሹመት ተቀብሎ ማጽደቁ ይታወሳል።

በዕለቱ  በምክር ቤቱ ቀርበው ከተሾሙት ሌሎች ሁለት ሹመኞች ጋር አቶ ገዱ ቀርበው ቃለ መሃላ አለመፈጸማቸው ይታወቃል።

በዛሬው ዕለትም አቶ ገዱ በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 111 መሰረት ዛሬ ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ፊት ቀርበው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት የተጣለባቸውን የህዝብና የመንግስት ሃላፊነት በቅንነት፣ በታታሪነትና ህግና ደንብን መሰረት በማድረግ ለመወጣት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎም ለአዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስኬታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

ከአቶ ገዱ ጋር የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ አይሻ አህመድ ደግሞ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ሹመታቸውም በአንድ ተቃውሞ በአምስት ድምጸ ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ በምክር ቤቱ ማጽደቁ ይታወሳል።