የደኢህዴን ህልውናን ለማረጋገጥ አመራሩ በትኩረት ሊንቀሳቀስ ይገባል”-ወ/ሮ ሙፈሪያት
የደኢህዴን ህልውና ለማረጋገጥ አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የድርጅቱ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ።
ክልል አቀፍ የደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት በሃዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
በምክክር መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ጊዜው በሀገርና በክልሉ የፖለቲካና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ወጥ አቋም ያለው አመራር ማፍራት የግድ የሚልበት ነው ብለዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር ወቅት የሚጠይቀውን ቁርጠኝነት ግምት ውስጥ ያስገባ ዝግጁነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ወይዘሮ ሙፈሪያት “በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለጸጥታውና ለምጣኔ ሀብት የሚኖረውን እንድምታ በመረዳት አመራሩ እራሱን ፈትሾ ለለውጥ ዝግጁ መሆን አለበት “ብለዋል።
ደኢህዴን ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው ይህን ለማስቀጠል ወቅቱን ተረድቶ በተገቢው መንቀሳቀስ እንደሚገባ አመልክተዋል።
“ምንም አይመጣም ብሎ በመኩራራትና ጨለማ ነው ብሎ በመስጋትም የሚመጣ ነገር የለም” ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት አመራሩ በአምስት ቀናት በሚኖረው ቆይታ በጥልቀት በመወያየት በድርጅቱ ቀጣይነት ላይ ተገቢውን አቋም ሊይዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሚቆየው የደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች የምክክር መድረክ በሀገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም በክልል እንሁን ጥያቄ ዙሪያ በተካሄደው ጥናት ላይ በመወያየት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ ፥ ኢዜአ