Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ደኢህዴን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የሲዳማና የሀድያ ዞን ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከኃላፊነት አገደ

0 2,163

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ደኢህዴን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የሲዳማና የሀድያ ዞን ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከኃላፊነት አገደ

(ኢ.ፕ.ድ)

ደኢህዴን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሲዳማ እና የሀድያ ዞን ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከኃላፊነት አደገ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ነው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎቹ ከስራ መታገዳቸውን ያስታወቀው።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በመግለጫው በክልሉ የሚነሱትን የክልልነት ጥያቄ የሚመለስበት አግባብ ላይ ግልጽ አቅጣጫ በድርጅቱ ጉባዔ መቀመጡን አስታውሶ፥ ይሁን እንጂ ከድርጅት አቅጣጫና ከመንግስት ውሳኔ በተቃራኒ የተፈጸሙ ኢ ህገ መንግስታዊ ድርጊት እና ይህንን ተከትሎ በሲዳማ ዞን በሰው ህይወት፣ አካል እና ስነ ልቦናዊ እንዲሁም በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ አሳዛኝ እና ኢ ሰብአዊ በመሆኑ በጽኑ አውግዟል።

የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች መጽናናትን የተመኘው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፥ በጥቃቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ በአስቸኳይ እንዲሰራም ወስኗል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በጥፋቱ የተሳተፉ እንዲሁም ያስተባበሩ እና የመሩ አካላትን ከህዝቡ ጋር በመተባበርና በመለየት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመሩት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ለፍጻሜ እንዲደርሱ በጥብቅ እንደሚሰራም አስታውቋል።

በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የስርዓት አልበኝነት አዝማሚያዎች በክልሉ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደረጉ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆሙና የህግ የበላይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቋም መወሰዱን በመግለጫው ተመልክቷል።

በዚህም የተነሳ በአካባቢው የሚታዩ የስርዓት አልበኝነት በህዝብ ጥያቄ ሽፋን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የክልሉን ህዝቦች ደህንነት ስጋት ላይ የጣሉ በመሆናቸው በመደበኛው የፀጥታ ስራ መቆጣጠር ወደማያስችልበት ደረጃ በመድረሱ የፀጥታው ስራ በፌደራል ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መደረጉንም አስታውቋል።

በክልሉ የሚከሰቱ ችግሮች በዋናነት ከአመራር ስርዓቱ ጋር የተያያዙ መሆኑን አስቀድሞ መገምገሙን በማስታወስ አሁንም ለተፈጠረው ችግር የአመራር ሚና የጎላ መሆኑን ተመልክቷል።

በቀጣይም ይህንን ለማረም ከድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ እና ማእከላዊ ኮሚቴ ጀምሮ እስከታችኛው የአመራር እርከን ድረስ ፈትሾ እርምት በመውሰድ ውጤቱን ለአባላቱና ለህዝቡ እንደሚያሳውቅ ውሳኔ አሳልፏል።

አሁን ችግሩ በተከሰተባቸው እና ህዝቡን ስጋት ውስጥ ያስገቡ እንቅስቀሴዎች ጎልተው እየታዩ መሆናቸውን በገመገመባቸው አካባቢዎች ካለፈው ጉድለቶች ትምህርት በመውሰድ በፍጥነት የአመራር ስርዓቱን ለማስተካከል የፖለቲካ ተጠያቂነቱን ማራጋገጥ መጀመሩን አስታውቋል።

በዚህ መሰረት ሰሞኑን በሀዋሳ ከተማና እና በሲዳማ ዞን የገጠር አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት የራሳቸው ሚና ነበራቸው በሚል የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እና የሲዳማ ዞን የፊት አመራሮችን ከመንግስትና ከድርጅት ሀላፊነት ያገደ መሆኑን አስታውቋል።

የሃድያ ዞንም የህዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ የተደረገውን እንቅስቃሴ በመገምገም በተመሳሳይ ሁኔታ የዞኑን የመንግስት አመራር ከሃላፊነት ማገዱን ደኢህዴን አስታውቋል።

በተጨማሪም በወላይታ ዞን አካባቢ ከመርህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ያሳሰበው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፥ በከፋ ዞንም የተካሄዱትን እንቅስቀሴዎች የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ናቸው ሲል አሳስቧል።

እንደ ኤፍ ቢ ሲ ዘገባ የክልሉ ህዝቦች ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከህግና ስርዓት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና ድርጊቶችን በመከላከልና በማጋለጥ ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ አቅርቧል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy