ሱዳንን ለ30 ዓመታት የገዛው የፕሬዚደንት አልበሽር መንግስት በሱዳን ወታደራዊ ኃይል ከስልጣን ከተወገደ ወዲህ ወታደራዊ ምክር ቤቱ ሀገሪቱን እየመራ ይገኛል:: ወታደራዊ ምክር ቤቱና ተቃዋሚ ኃይሎች በተደጋጋሚ ስልጣን ለመጋራት ቢደራደሩም ሳይሳካ ቆይቷል:: በተለይም የአፍሪካ ሕብረትና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተጫወቱት ቁልፍ ሚና በመጨረሻ ወታደራዊ ምክር ቤቱና የተቃዋሚዎች ሕብረት ከስምምነት ላይ በመድረስ የተፈጠረውን ሀገራዊ ሁከትና ትርምስና ለማስቆም አብረው በጋራ ለመስራት ተስማምተው ተፈራርመዋል::
የተቃዋሚ መሪዎችና ወታደራዊ ምክር ቤቱ አንድ ሌሊት የዘለቀ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው ስምምነት ላይ ደርሰዋል:: ይህን ወቅታዊ ጉዳይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ሚና የጎለበትን ዘገባ በመያዝ ቢቢሲ፤ ሲኤንኤን፤ አሶሽየትድ ፕሬስ፤ ዥንዋ፤ አጃንስ ፍራንስ፤ አልጀዚራና ሌሎችም በስፋት ለንባብ አብቅተውታል::
ስምምነቱ የተፈጸመው ለሀገሪቱ ታሪካዊ በሆነ ወቅት ነው በሚል የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሞሀመድ ሀምዳን “ሄምቲ” ዳጎሎ ለአንድ የግል የዜና ወኪል የሰጡት መግለጫ ተደጋግሞ በመጠቀስ ላይ ይገኛል:: ባለፈው ሚያዝያ ወር ወታደሩን ጨምሩ የሲቪል መንግስት ለመመስረት ሲተጉ የነበሩት ኃይሎች ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን ካስወገዱ ወዲህ ሱዳን ከፍተኛ ነውጥ ውስጥ ነች ብለዋል ጀነራሉ::
ልክ እንደ ግብጹ የታህሪር አደባባይ ሀገር ያናወጠ የተቃውሞ ሰልፍና የመቀመጥ አድማ አይነት ከሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ፊት ለፊት ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች ወታደሩ ለሲቪሎች ስልጣኑን እንዲያስረክብ ሲጠይቁ ነበር:: እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ሰኔ 3 በከፍተኛ ሁኔታ ተመተዋል:: 128 ሰዎች ተገድለዋል:: ወታደራዊ ባለስልጣናቱ ሪፖርቱን አይቀበሉም:: ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ሕብረት ታላቅ የሰላምና የድል ስኬት ተደርጎ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እየተወደሰ ያለው የሁለቱ ወገኖች ስምምነት የደረሰበት አንዱ መደምደሚያ ምክር ቤቱን በፈረቃ መምራት ነው::
ምክር ቤቱ ከፍተኛውና የመጨረሻው የስልጣን እርከን ነው:: በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ በፈረቃ ይመራል:: በመጨረሻም በምርጫ ለሚመሰረት የሲቪል መንግስት በሰላም ስልጣኑን ያስረክባል:: የሀገሪቱ መሪ የሆነው ምክር ቤት በአምስት ሲቪሎችና በአምስት ወታደራዊ ጀነራሎች ይዋቀራል:: አስራ አንደኛ የሚሆነው ሲቪል ደግሞ በአስሩ አባላት ይመረጣል::
ለመጀመሪያዎቹ 21 ወራት የምክር ቤቱን አመራር ወታደራዊ ጀነራል ይይዛል:: ለቀጣዩ 18 ወራት ደግሞ ምክር ቤቱ በሲቪል ይመራል:: በኋላም ምርጫ ይከተላል:: ወታደራዊ አመራሩ ለተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በወሰደው እርምጃ በርካታ ሱዳናውያን ተገድለዋል:: ከዚህ ክስ ነጻ እንዲሆን ግፊት ቢያደርግም በስምምነቱ ውስጥ አልተካተተም:: ቢሆንም ጉዳዩ እንዲመረመር ቃል ገብቶአል::
ሁለተኛው ስምምነት የሕገ መንግስት ጉዳዮችን የሚመለከት ሲሆን በቀጣዩ ዓርብ እንደሚጠቃለል ይጠበቃል:: ወራትን ካስቆጠረ ብልጭ ድርግም ከሚል ንግግርና ውይይት በኋላ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት መፈራረማቸው በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው::
በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ስምምነቱ ማለት ሱዳን ከ30 ዓመታት ወታደራዊ አገዛዝ በኋላ ሙሉ በሙሉ ሲቪላዊ ለሆነ የሕዝብ አስተዳደር ሶስት ዓመት ብቻ ይቀራታል ማለት ነው::
የስምምነቱ ዝርዝሮች አልተገለጹም:: ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ገና ውይይት ይካሄድባቸዋል እንጂ ስምምነት አልተደረሰባቸውም:: አሁንም ቢሆን ሀገሪቱን በሽግግሩ ውስጥ የሚመራ ነጻ ምክር ቤት መሾም አለበት:: ከበርካታው ተቃዋሚ ውስጥ የተደረሰበትን ስምምነት ምናልባት ጥቂቶች የዱላው አጭር ማብቂያ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ::
እነሱ የተናነቁትና የታገሉት ወታደራዊ ኃይል በጎዳናዎች ላይ የተሰቃዩበትና የተገደሉበት አሁን በስልጣን ላይ ነው:: የሽግግር መንግስቱን ይመራል:: ጀነራሎቹ ያለመከሰስ መብታቸውን ያስጠብቃሉ:: በተቃዋሚዎቹ ዓይን ፍትህ ገና ስራ ላይ አልዋለም:: ቢሆንም ስርአቱን ለመጣል የዘመሩት መዝሙር ወደአሁኑ አዲስ መንገድ አድርሷቸዋል::
በሱዳን አለመረጋጋት የተፈጠረው ወደኋላ ሲቆጠር ከታህሳስ 2018 ጀምሮ ነበር:: የያኔው የፕሬዚደንት በሽር መንግስት አስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጆ እርምጃዎችን ተግባራዊ አድርጓል:: በሚያዝያ ወር ካርቱም በሚገኘው የሱዳን መከላከያ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ከተደረጉ በኋላ ወታደሩ ፕሬዚደንቱን ከስልጣን አወረደ:: የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ስልጣን በሰላም ወደ ሲቪል አስተዳደር መዛወሩን ማረጋገጥ ፈልገው ነበር::
ተቃዋሚው ሰልፈኞች ከመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውጭ ሆነው ቆዩ:: በኋላም ሰኔ 3 የፈጥኖ ደራሹ ኃይል፤ ፓራሚሊተሪውና፤ የወታደራዊ ምክር ቤቱ እዝ የተከማቹትን ሰልፈኞች ለመበታተን ተንቀሳቀሰ:: በርካቶች ተገደሉ:: አስከሬናቸው ወደ ናይል ወንዝ ተወረወረ:: ተንታኞች እንደሚገልጹት በዚያን እለት ከ300 በላይ ቪዲዮዎች የተቀረጹ ሲሆን በሙሉ የሚያሳዩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በእውነተኛ ጥይት በተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ላይ ሲተኩስ የነበረ መሆኑን ነው::.
ጭፍጨፋና ግድያው ከተካሄደ ከሳምንት በኋላ ዳግም በብዙ 10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ:: ከተማዋን አጥለቀለቋት:: በዚህ መነሻነት ነው ወታደራዊው ጁንታ ለተቃዋሚው ስልጣን በማጋራት የጋራ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ውይይት ውስጥ ለመግባት የተገደደው::
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አመራር ለተፈጸመው ግድያ ኃላፊነት የለብኝም ሲል ክዷል:: ሌሎች ናቸው ግድያውን የፈጸሙት ብሏል:: የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ራሱ ተኮትኩቶ ያደገው ከጃንጃዊድ ሚሊሺያ ውስጥ ነው:: የጃንጃዊድ ሚሊሺያ በምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ግዛት የዘር ማጥፋት ግድያ በመፈጸም ክስ ሲቀርብበት ነበር::
በአጠቃላይ ዶ/ር ዐቢይና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን የሰላም ድርድር ጉዳይ የተሳካላቸው መሆኑን በመግለጽ የዓለም መሪዎችና መገናኛ ብዙሀን አወድሰዋል:: በጣም ውጥረት ከበዛበት የወራት ድርድር በኋላ የሱዳን ተቃዋሚዎች ሕብረትና የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ካርቱም ውስጥ የፖለቲካ ስምምነት ተፈራርመዋል::
ሕገ መንግስታዊ አዋጅ ተብሎ በሚታወቀው ሁለተኛው ሰነድ ላይ ውይይቱ ይቀጥላል:: የሱዳን ተቃዋሚዎች ሁለቱን ተቃቅረው የነበሩትን ወገኖች በማቀራረብ የተሳካ ውጤት ለማስገኘት ባሳለፉት ጠንካራ ስራ የአፍሪካ ሕብረትና የኢትዮጵያን አደራዳሪዎች አመስግነዋል::
በሰኔ 7 ቀን 2019 የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአፍሪካ ሕብረት ድጋፍ የሱዳን ኃይሎችን ለማደራደር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በዚህም አንዱን ከፍተኛ ዲፕሎማታቸውን አምባሳደር መሀመድ ድሪርን የእሳቸው ተወካይ ልዩ ልዑክ አድርገው በመሾም የተሳካ ውጤት ለማስመዝብ በቅተዋል:: ይህን ተነሳሽነትና ስኬት የዓለም መሪዎች አወድሰውታል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በሰሯቸውን የሰላም እና የእርቅ ስራዎችን ተከትሎ 12 የሚደርሱ ሽልማቶችን አግኝተዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ያላቸው ቁርጠኛ አቋም ስኬታማነቱ ኢትዮጵያን ከኤርትራ አንድ ያደረጋትን ተግባር ጨምሮ የሱዳን ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ እና አለመስማማት በሰላም መቋጨት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳካ የሰላም ስራ ሌላው ማሳያ ነው::
የተፈረመው ሰነድ ሱዳንን ለ39 ወራት የሚያስተዳድር የሽግግር ሂደት ነው:: በተፈረመበት ፍሬንድሽፕ አዳራሽ አካባቢ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በመገኘት ደስታውን ገልጿል:: ወደ ሲቪል አስተዳደር የሚያሻግር ታሪካዊ ሰነድ መሆኑን ዘገባዎች ያስገነዝባሉ::1