በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለኮቪድ-19 መከላከያ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚሆን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉ በብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ስር የተቋቋመው የውጭ ድጋፍ አሰባሰቢ ንኡስ ኮሚቴ አስተባባሪነት መሰብሰቡም ተገልጿል።
ኮሚቴው ባለፉት ሳምንታት ከተለያዩ ሃገራት ሃብት የማሰባሰብ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በተለያዩ የዓለም አገራት የተቋቋሙ 60 የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች የኮሚቴውን እቅድ መነሻ በማድረግ በልዩ ልዩ ደረጃዎች ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙም ተገልጿል።
በመሆኑም በመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የየሚሲዮኖቹ ሰራተኞች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ኢዜአ ዘግቧል።