Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንዲተረጉማቸው ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወሰኑት የሕገ መንግስቱ ሦስት አንቀፆች ምን ይላሉ??

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንዲተረጉማቸው ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወሰኑት የሕገ መንግስቱ ሦስት አንቀፆች ምን ይላሉ??

0 83,979

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንዲተረጉማቸው ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወሰኑት የሕገ መንግስቱ ሦስት አንቀፆች ምን ይላሉ??
*************

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 83 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የምርጫው መራዘምን በተመለከተ ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን አንቀፆች እንዲተረጉም ወስኗል፡፡

በዚህም ውሳኔ መሰረት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የህግ ትርጓሜ የሚሰጣቸው የህገ መንግስቱ አንቀፆች አንቀፅ 54/1 አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 93 ናቸው።

በሕገ መንግስቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚለው ርእስ ስር

አንቀጽ 54 – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

1. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፡፡

አንቀጽ 58 – የምክር ቤቱ ስብሰባና የሥራ ዘመን

3. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሒዶ ይጠናቀቃል፡፡

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

አንቀጽ 93 – ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

1. ሀ) የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡

ለ) የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ። ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገ መንግሥቶች ይወሰናል፡፡

2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መሠረት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤

ሀ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል፡፡

ለ) ከላይ በንዑስ አንቀጽ(ሀ) ስር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡

3. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደረግ ይችላል፡፡

4. ሀ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
ለ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ፣ እስከማገድ ሊደርስ የሚችል ነው፡፡

ሐ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

5. በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል፡፡ ቦርዱ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚጸድቅበት ጊዜ ይቋቋማል፡፡

6. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች አሉት፤

ሀ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፣

ለ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፣

ሐ) ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሀሳብ መስጠት፣

መ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣

ሠ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ማቅረብ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy